ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና እና መቻል ነጥብ ተጋርተዋል

ተጠባቂ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና መቻል ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 1-1 ተጠናቋል።

በሳምንቱ ተጠባቂ መርሐግብር ኢትዮጵያ ቡና እና መቻል ተገናኝተው ቡናማዎቹ በ21ኛው ሳምንት በአዳማ ከተማ 1ለ0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የአንድ ተጫዋች ለውጥ ራምኬል ጀምስ በወልደአማኑኤል ጌቱ ተተክቶ ገብቷል። መቻሎች በአንጻሩ በኢትዮጵያ መድን 2ለ1 ከተሸነፉበት ስብስብ ባደረጉት የአንድ ተጫዋች ለውጥ ባለፈው ሳምንት በቅጣት ያልነበረው ዳዊት ማሞ ዛሬ በዮዳሄ ዳዊት ተተክቶ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ ተመልሷል።

10፡00 ላይ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ዶክተር ኃይለኢየሱስ ባዘዘው ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ ፈጣን አጀማመር ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች 7ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው አማኑኤል አድማሱ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው መስፍን ታፈሰ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ቡናማዎቹ ተጭነው መጫወታቸውን በመቀጠልም ከመስፍን ታፈሰ ሙከራ ከሴኮንዶች በኋላ አብዱልከሪም ወርቁ ከአንተነህ ተፈራ ጋር ተቀባብሎ በወሰደው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን አስወጥቶበታል። ያንኑ ኳስም ራሱ አብዱልከሪም ወርቁ በቀኝ መስመር ከማዕዘን አሻምቶት ኳሱን ያገኘው ዋሳዋ ጄኦፍሪ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ግለት የገቡት መቻሎች 20ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ምንይሉ ወንድሙ ግብ ጠባቂውን በረከት አማረን ለማለፍ ሲሞክር በተሠራበት ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት በተረጋጋ ሁኔታ ግብ ጠባቂው እንደቆመ ኳሱን በቀኝ በኩል መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በሁለቱም በኩል በሚደረጉ ፈጣን ሽግግሮች ብርቱ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ በቡናማዎቹ በኩል 32ኛው ደቂቃ ላይ በፍቃዱ ዓለማየሁ ከመስፍን ታፈሰ በተቀበለው ኳስ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ የመለሰበት እና በመቻል በኩል ደግሞ 34ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ከሳጥን አጠገብ ሞክሮ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ የመለሰበት ኳስ ተጠቃሽ ነበሩ።

መቻሎች 37ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አቤል ነጋሽ በሰነጠቀለት ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ከማቀበል አማራጭ ጋር ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው ከነዓን ማርክነህ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብለት ቀርቶ ወርቃማውን የግብ ዕድል አባክኖታል። ሆኖም 45+5ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች ወሳኝ ጎል አግኝተዋል። ዋሳዋ ጄኦፍሪ በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ኳሱን ያገኘው አማኑኤል አድማሱ ከሳጥን አጠገብ ከፍ አድርጎ በመምታት አስቆጥሮታል።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች በመረጡት ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በሁለቱም በኩል በርካታ ቅያሪዎች ቢደረጉም ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 1-1 ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች በቅጣት ምክንያት ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ቡድናቸውን የመሩት የመቻሉ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች የቦታ አያያዝ ትልቅ ድክመት እንዳለባቸው ጠቅሰው የልምምድ መስሪያ በቂ ቦታ እና ጊዜ እንደሌለም በመግለጽ በአቻ ውጤቱም እንዳልተከፉ ተናግረው ለመጫወቻ ሜዳው መስተካከልም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ሁኔታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም የአጨራረስ ችግር እንደነበረባቸው ሆኖም ከዕረፍት መልስ ግን ተጫዋቾቻቸው በዓየር ንብረቱ ምክንያት ድካም እንደተስተዋለባቸው ገልጸው ለመጫወቻ ሜዳው የከተማ አስተዳደሩን እና ከንቲባውን አመስግነዋል።