ሪፖርት| ተጠባቂው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

ዐፄዎቹና የጣና ሞገዶቹ ያደረጉት ጨዋታ በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ጎል አልባ የአቻ ውጤት ተመዝግቦበታል።

ዐፄዎቹ ከኋላ ተነስቶ ሀድያ ሆሳዕናን ካሸነፈው ቀዳሚ አሰላለፍ ቃልኪዳን ዘላለምን በአቤል እንዳለ ተክተው ሲገቡ የጣና ሞገዶቹ በበኩላቸው ድሬዳዋ ከተማን ካሸነፈው አሰላለፍ ፍፁም ፍትሕዓለው ፣ ፍሬው ሰለሞና እና ቸርነት ጉግሳን በያሬድ ባየህ ፣ አባይነህ ፊኖና ጸጋዬ አበራ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ተመጣጣኝ ፉክክር ፣ በርከት ያሉ የአንድ ለአንድ ፍልምያዎች እና የተከላካዮች የግል ስህተቶች የተስተዋለበት የመጀመሪያው አጋማሽ ምንም እንኳን በርከት ያሉ ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ባይደረጉም የጨዋታውን መልክ ሊቀይሩ የሚችሉ የግብ ዕድሎች ተፈጥረውበታል። በአመዛኙ በቀጥነኛና ፈጣን ሽግግሮች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ባህርዳር ከተማዎች በፀጋዬ አበራ እና ሀብታሙ ታደሰ ሙከራዎች መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በተለይም ሀብታሙ ታደሰ ፍራኦል መንግሥቱ ከግራ መስመር ያሻማትን ኳስ በግሩም የመጀመርያ ንክኪ አብርዶ የሞከራት ኳስ የጣና ሞገዶቹን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

ጨዋታውን ለመቆጣጠር ብርቱ ፍላጎት የነበራቸው ዐፄዎቹ በአጋማሹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ቢይዙም በአጨዋወቱ ንፁህ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በአጋማሹም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አላደረጉም። ሆኖም በተጋጣሚ ስህተት ባገኛቸው ሁለት ኳሶች ጨዋታውን ለመምራት ተቃርበው ነበር። ጃቢር ሙሉ እና ፍቃዱ ዓለሙ በተከላካዮች ስህተት አግኝተውት በውሳኔ አሰጣጥ ችግር ያመከኗቸው ሁለት ኳሶችም በዐፄዎቹን በኩል ከታዩ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።

ሁለተኛው አጋማሽ በፋሲል ከነማ ብልጫ ቢጀምርም ብልጫው ለረዥም ደቂቃዎች መዝለቅ አልቻለም። ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመርያው አጋማሽ አቀራረባቸው ላይ ለውጥ ያላደረጉበት አጋማሽ ምንም እንኳ በዐፄዎቹ ብልጫ ቢጀምርም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ሄዶ አደጋዎች በመፍጠር ረገድ ግን ጣና ሞገዶቹ የተሻሉ ነበሩ። ከግሩ አፋፍ የነበረው ሀብታሙ ከመሳይ የተሻገረለትን ኳስ መቶት ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ውጭ ያወጣው ኳስም የጣና ሞገዶቹን መሪ ለማድረግ ተቃርቦ ነበር። ጨዋታው መሀል በተከሰቱ ጉዳቶችና ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ ታጅቦ ቢቀጥልም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የፉክክር መንፈሱ ሳቢ ነበር።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተለየ ፍላጎት ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ባህርዳር ከተማዎች በአስራ አንደኛው ሰዓት አሸንፈው የሚወጡባቸው ሦስት አጋጣሚዎች ቢያገኙም ኳስና መረብ የሚስታርቅ ተጫዋች ማግኘት አልቻሉም። ሀብታሙ ታደሰ ከግራ መስመር ያተሻገረች ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ያደረጋት ኳስና ተቀይሮ የገባው ወንድወሰን ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከናት ኳስም የማታ ማታ ሞገዱን አሸናፊ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሀሳባቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጨዋታው ከባድ እንደነበር ገልፀው ከተጋጣሚያቸው ጥንካሬ እና ደርቢ ከመሆኑ አንፃር በውጤቱ እንደማይከፉ አንስተዋል አሰልጣኙ ጨምረውም በሁለተኛው አጋማሽ ያጋጠሟቸው ጉዳቶች የቡድኑ እንቅስቃሴ እንዳወረደው ገልፀዋል። የባህርዳር ከተማ ምክትል አሰልጣኝ መብራቱ ሀብቱ በበኩላቸው በጨዋታው በርከት ያሉ ዕድሎች ቢፈጥሩም አፈፃፀም ላይ ክፍተቶች እንደነበሩባቸው ገልፀዋል።