ሪፖርት | ሀምበርቾ 19ኛ ሽንፈት አስተናግዷል

የጣና ሞገዶቹ በፍጹም ጥላሁን ሁለት ግቦች ሀምበርቾን 2ለ0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሰዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ሀምበርቾ እና ባህር ዳር ከተማ ተገናኝተው ሀምበርቾዎች በ24ኛው ሳምንት በመቻል 2ለ0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ታየ ወርቁ እና ታሪኩ ታደለ ወጥተው ትዕግስቱ አበራ እና ሙና በቀለ ገብተዋል። የጣና ሞገዶቹ በአንጻሩ ከፋሲል ከነማ ጋር 0-0 ከተለያዩበት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ መሳይ አገኘሁ ፣ ያሬድ ባዬህ እና ፍሬው ሰለሞን ወጥተው ረጀብ ሚፍታህ ፣ ፍጹም ፍትሕዓለው እና ዓባይነህ ፌኖ ገብተዋል።


የሀምበርቾ ተጫዎቾች በደመወዝ ይከፈለን ጥያቄ ከጨዋታ በፊት ባለው የሰውነት ማሟሟቂያ ላይ ለመገኘት ፍላጎት ሳይኖራቸው ቀርቶ አብዱልከሪም ዱግዋ እንዲሁም ግብ ጠባቂዎቹ ፖሉ ፖጁ እና ምንታምር መለሰ ካሟሟቁ በኋላ ቡድኑ ጨዋታውን አያደርግም ተብሎ ሲጠብቅ የኋላ ኋላ በመልበሻ ክፍል ውስጥ በተደረሰ መግባባት በቋሚ አሰላለፍ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ ገብተዋል።

9፡00 ሲል በዋና ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ ገና በ3ኛው ደቂቃ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ሀብታሙ ታደሰ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) የመታው ኳስ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቶ ወርቃማውን ዕድል ሲያባክነው አጥቂው ከደቂቃዎች በኋላም ከየአብሥራ ተስፋዬ በተመቻቸለት ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ኳሱን አስረዝሞ ገፍቶት አባክኖታል።

ባህር ዳር ከተማዎች በሚያገኙት ኳስ ሁሉ ቶሎ ቶሎ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ 16ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ንጹህ የግብ ዕድል ፈጥረው ጸጋዬ አበራ ከሀብታሙ ታደሰ በተቀበለው ኳስ በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ ይዞበታል። በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ የአብሥራ ተስፋዬ ከፍጹም ጥላሁን በተመቻቸለት ኳስ ያደረገውን ሙከራ ፖሉማ በግሩም ቅልጥፍና አስወጥቶታል።

ሀምበርቾዎች ገና በ23ኛው ደቂቃ አማካያቸውን በኃይሉ ተሻገርን በጉዳት ምክንያት አስወጥተው በበፍቃዱ አስረሳኸኝ አማካኝነት ለመቀየር ሲገደዱ በ24ኛው እና 27ኛው ደቂቃ ላይ በሀብታሙ ታደሰ አማካኝነት ሙከራ ከተደረገባቸው በኋላ 28ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን ፈጥረው አልዓዛር አድማሱ በሳጥኑ የግራ ክፍል በጥሩ ሁኔታ ገፍቶ የወሰደውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲቀንሰው ንቁ የነበረው ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ይዞበታል።

እየተቀዛቀዘ የሄደው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ አራት ደቂቃዎች ውስጥ የመጀመሪያው ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶቹ ግብ አስቆጥረዋል። ፍጹም ጥላሁን ከሳጥን አጠገብ የመታው ኳስ በትዕግስቱ አበራ ተጨርፎ አቅጣጫ በመቀየር ግብ ሆኗል።

ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል ባህር ዳሮች 50ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን ለማጠናከር ተቃርበው ረጀብ ሚፍታህ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ፍጹም ጥላሁን በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ መልሶበታል።

ሀምበርቾዎች የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራቸውን 51ኛው ደቂቃ ላይ አድርገው አብዱልከሪም ዱግዋ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ተጨርፎ ወደ ጎል ሲያመራ የመሃል ተከላካዩ ፍሬዘር ካሳ ራሱን አደጋ ላይ በመጣል ኳሱን በግንባር ገጭቶ አስወጥቶታል። በአጋጣሚውም ከግቡ የቀኝ ቋሚ ጋር ሳይጋጭ መቅረቱ ዕድለኛ አድርጎታል።

የጣና ሞገዶቹ ተጨማሪ ግብ ፍለጋ በመታተር አጥቅተው መጫወት ሲችሉ 68ኛ ደቂቃ ላይ በሀብታሙ ታደሰ ጥሩ ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ ሲመለስባቸው ያንኑ ኳስ ያገኘው ፍጹም ጥላሁንም በግብ ጠባቂው እግር መሃል (ሎጬ) የላከውን ኳስ አዲስዓለም ተስፋዬ ከመስመር አግዶታል። ሆኖም 72ኛው ደቂቃ ላይ ግን ተሳክቶላቸዋል። ዓባይነት ፌኖ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ፍጹም ጥላሁን ኳሱን ዓየር ላይ እንዳለ በመምታት በግሩም ሁኔታ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ብልጫ ይወሰድባቸው እንጂ ካለፈው ሳምንት ጨዋታቸው አንጻር ተሻሽለው የቀረቡት ሀምበርቾዎች በጨዋታው የተሻለውን የግብ ዕድል 79ኛው ደቂቃ ላይ ፈጥረው አብዱልከሪም ዱግዋ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ሲያስወጣበት ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ያገኘው አልዓዛር አድማሱ በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራም ፔፔ ሰይዶ በድጋሚ ይዞታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ጨዋታው መጠነኛ ፉክክር ተደርጎበት በባህር ዳር ከተማ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀምበርቾው አሰልጣኝ ብሩክ ሲሣይ ተጫዋቾች ካላቸው ጥያቄ አንጻር ከተፈጠረባቸው ጫና ተላቅቀው መፋለማቸውን አድንቀው ማሟሟቂያ ላይ ላልነበሩ ተጫዋቾች ቡድኑ የቻለውን ማድረጉ ለመጫወታቸው ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰው ላለመውረድ በሚደረገው ትንቅንቅ ሌሎች ቡድኖች ነጥብ እየጣሉ ቢሆንም አጋጣሚውን መጠቀም እንዳልቻሉ ሲናገሩ የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በበኩላቸው ውጤቱን ከመፈለግ አንጻር ተጫዋቾች ላይ ጉጉት እንደነበር እና የሀምበርቾ ተጫዋቾች ይጫወታሉ ወይስ አይጫወቱም በሚለው ጉዳይ ትኩረት ማጣት እንደፈጠረባቸው ጠቁመው በመሳይ አገኘሁ ተተክቶ የገባውን የረጀብ ሚፍታህን እንቅስቃሴ አድንቀዋል።