መረጃዎች | 103ኛ የጨዋታ ቀን

እጅግ ወሳኝ ወደሆነው ምዕራፍ እየተሸጋገረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በ26ኛ ሳምንት መርሃግብር ይመለሳል ፤ የነገዎቹን ሁለት መርሃግብሮች የተመለከቱ መረጃዎችን አነሆ።

ወልቂጤ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ መርሃግብር የወራጅነት ስጋት የተደቀነባቸውን ወልቂጤ ከተማዎችን ደካማ ወቅታዊ ብቃት ላይ ከሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎችን የሚያገናኝ ይሆናል።

በ16 ነጥቦች በሰንጠረዡ 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች እጅግ አስቸጋሪ ጊዜን እያሳለፉ ይገኛሉ ፤ በሊጉ ባደረጓቸው የመጨረሻ አምስት የሊግ ጨዋታዎችን በሙሉ የተሸነፉ ሲሆን ከውጤት ባሻገርም የቡድኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴም አመርቂ ስላለመሆኑ እየተመለከትን እንገኛለን።

በሰንጠረዡ በ3 ነጥብ ርቀት 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሻሸመኔ ከተማዎች ምንም እንኳን የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ቢያደርጉም ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ያለመቻላቸው ጉዳይ ወልቂጤ ከተማን በእጅጉ የጠቀማቸው ይመስላል እንጂ እንደ ሰሞነኛ ብቃታቸው ረዘም ላሉ ሳምንታት ተቆናጥው በቆዩት 14ኛ ደረጃ የመቆየታቸው ነገር የሚሳካ አልነበረም።

በአንፃሩ በ34 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች በከተማቸው በነበረው የሊጉ ቆይታ ከነበራቸው መነቃቃት በኃላ ወደ ሀዋሳ ከመጡ ወዲህ ግን ነገሮች መልካቸውን እየቀየሩ ያለ ይመስላል።

ቡድኑ በሀዋሳ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሽንፈት ሲያስተናግድ በአንዱ ብቻ ነጥብ ተጋርተዋል ፤ በእነዚህም ጨዋታዎች ቡድኑ አንድ ግብ ብቻ ሲያስቆጥሩ በአንፃሩ ሰባት ግቦችን አስተናግደዋል። በተለይም በመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ መድን የደረሰባቸው የ5-0 ሽንፈት እጅግ አሰቃቂው ነበር።

ይህም ሽንፈት በ2014 የውድድር ዘመን በ15ኛ የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ በፋሲል ከነማ ከደረሰበት የ4-0 ሽንፈት በኃላ የተመዘገበ አስከፊ ውጤት ሲሆን አሰልጣኝ ሽመልስ አበበ ከዚህ አስከፊ ሽንፈት ማግስት በስነልቦና ረገድ ዝቅታ ላይ የሚገኘውን ስብስብ አነሳስቶ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ የማድረግ የቤት ስራቸውን እንዴት እንደሚወጡ ይጠበቃል።

በወልቂጤ ከተማ በኩል ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ ከሦስት ጨዋታዎች ቅጣት በኋላ ይመለሳል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 7 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን እኩል ድሬዳዋ ሶስት እንዲሁም ወልቂጤ ሁለት ጊዜ ባለድል ሲሆኑ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ወጥተዋል። ወልቂጤ 9 ፣ ድሬዳዋ 9 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ አዳማ ከተማ

የምሽቱ መርሃግብር ደግሞ ሁለት እጅግ አስደናቂ ብቃት ላይ የሚገኙ ቡድኖችን የሚያገናኝ ይሆናል።

በፈተና ከተሞላው የ2016 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ዙር በኃላ ኢትዮጵያ መድኖች እጅግ ወሳኝ በሆነው የውድድር ዘመኑ ወቅት እጅግ አስደናቂ ብቃት ላይ ተገኝተዋል ፤ በመጨረሻ አምስት የሊግ ጨዋታዎች በሙሉ በድል የተወጡት ኢትዮጵያ መድኖች አሁን ላይ በ31 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በእነዚህም አምስት ጨዋታዎች 13 ግቦችን ያስቆጠረው ቡድኑ በአንፃሩ ያስተናገዱት የግብ መጠን አንድ የመሆኑ ጉዳይ ኢትዮጵያ መድኖች ስለሚገኙት አስደናቂ ብቃት ገላጭ ቁጥሮች ናቸው።በተጨማሪም ከግብ ቁጥሮቹ ባለፈ በመጀመሪያው ዙር ብዙ ጥያቄ ይነሳበት በነበረው የቡድኑ የፊት መስመር ላይ በአጋማሽ የዝውውር መስኮት የተጨመሩ ተጫዋቾች የቡድኑ ማጥቃትን በሂደት የማሻሻላቸው ጉዳይ ሌላው ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው።

በመጨረሻ አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት ያላስተናገዱት አዳማ ከተማዎች በሦስቱ ድል ሲያደርጉ በሁለቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል ፤ ይህም የሰበሰቡትን ነጥብ ወደ 41 በማሳደግ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በተለያዩ ምክንያቶች በተጫዋቾች ጥራት ሆነ በብዛት ረገድ የተወሰኑ ውስንነቶች ውስጥ ሆኖ ውድድሩን ለመቀጠል የተገደዱት አዳማ ከተማዎች ግምቶችን በማፋለስ በተለያዩ ጨዋታዎች የመሰለፍ ዕድልን እያገኙ የሚገኙ አዳዲስ ተጫዋቾች ራሳቸውን በሚገባ እያሳዩ ቡድናቸውን እየጠቀሙ ያሉበት መንገድ አስገራሚ ሲሆን ከዚህ ባለፈ በቡድኑ ውስጥ ያለው ህብረት እንዲሆም ያለን ነገር በሙሉ ሜዳ ላይ ለመስጠት ያለ ተነሳሽነት እጅግ የተለየ ነው።

በአዳማ ከተማ በኩል ግብ ጠባቂያቸውን ሰዒድ ሀብታሙን በቅጣት እንዲሁም ሁለገቡን የተከላካይ መስመር ተሰላፊ አህመድ ረሺድን በጉዳት በነገው ጨዋታ እንደማያገኙ ተረጋግጧል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ 20 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አዳማ 7 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። መድን 3 ሲያሸንፍ 11 ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ ፤ አዳማ 25 ሲያስቆጥር መድን 20 አስቆጥረዋል። በዚህ ግንኙነት አዳማ በመድን ሽንፈት ካስተናገደም 20 ዓመታት ተቆጥረዋል።