መረጃዎች | 104ኛ የጨዋታ ቀን

በ26ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የሚደረጉ ሁለት መርሀ-ግብሮችን አስመልክተን ያሰናዳናቸው መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

መቻል ከ ሻሸመኔ ከተማ

በሰንጠረዡ አናት እና ግርጌ የሚገኙት ቡድኖችን የሚያገናኛውና ለዋንጫ እንዲሁም ላለመውረድ በሚደረገው ፍልምያ ትልቅ ትርጉም ያለው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ሦስት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ነጥባቸውን ሀምሳ ያደረሱት መቻሎች ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሆኑ አስመስክረዋል።

በባለፈው ሳምንት የቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችን ለመጥቀስ እንደሞከርነው የጦሩ የማጥቃት አጨዋወት በብዙ መልክ ጎልብቶ አስፈሪነት ተላብሷል። እዚህ ላይ በዋነኘነት ሊጠቀስ የሚገባው ግን አማካዮቹ በማጥቃት ሂደቱ ላይ ያላቸው ጉልህ አስተዋጾ ነው። በተለይም በቅርብ ሳምንታት ለአማካዮቹን ይበልጥ የማጥቃት ነፃነት የሰጡት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ውሳኔያቸው የፊት መስመሩን ጥንካሬ ከመጨመር አልፎ የግብ ምንጮቻቸውንም አስፍቶታል። አማካዮቹ በተለይም ባለፉት ሁለት መርሀ-ግብሮች የነበራቸው ተሳትፎና ያስቆጠሩት የግብ መጠንም የዚህ አንድ ማሳያ ነው።

ከቀደሙት ጊዜያት አንፃር በቁጥር በርከት ብሎ የሚታየው የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ደጋግሞ የመፍጠር ሂደት በነገው ጨዋታም በመቻል በኩል የሚጠበቅ ጠንካራ ጎን ቢሆንም የመከላከል አደረጃጀቱ ግን ለውጦች እንደሚሻ ምልክቶች አሉ።

ጦሩ በማጥቃቱ ግልፅና የሚታይ በጎ ለውጦች ማምጣት ቢችልም የመከላከል አደረጃጀቱ ጥንካሬ መላላት ግን ለዋንጫ በሚያደርገው ጉዞ ትልቅ ስጋቱ ነው። ቡድኑ አጥቅቶ በመጫወት ድፍረት ውስጥ ሆኖ ወደ ሜዳ ሲገባ በእንቅስቃሴ ለሚፈጠሩ ክፍተቶች ሁነኛ መፍትሄ ማግኘትም ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚጠበቅ ትልቅ የቤት ሥራ ነው። የተከላካይ መስመሩ ፈጣንና ሰፊ የመጫወቻ ክፍት ቦታዎች በአግባቡ ከሚጠቀሙ ቡድኖች በሚገጥምበት ወቅት የሚታይበት የንቃትና ፍጥነት እንዲሁም ደካማ የመከላከል ውሳኔዎች መቅረፍ ቀዳሚ ሥራው መሆን ይኖርበታል። የተጠቀሱት ክፍተቶች በኢትዮጵያ ቡናውና በመጨረሻው የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በጉልህ የታዩ ክፍተቶች ነበሩ። የነገው ተጋጣሚያቸው ሻሸመኔ ከተማ በቅርብ ሳምንታት ያሳየው ለውጦችም ጦሩ የመከላከል አደረጃጀቱን በድጋሜ እንዲከልስ የሚያስገድደው ሌላው ምክንያት ነው።

በአስራ ሦስት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሻሸመኔ ከተማዎች በቅርብ ሳምንታት በብዙ ረገድ ተሻሽለው ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም ካሉበት ደረጃ ፈቀቅ ማለት አልተቻላቸውም።

ሻሸመኔ ከተማዎች ባለፉት አራት ጨዋታዎች ተከታታይ ሽንፈቶች ብያስተናግዱም በጊዜ ሂደት የተሻሻለው እንቅስቃሴያቸው ከከባዱ ጨዋታ በፊት በሥነ ልቦናው ጠንክረው እንዲቀርቡ የሚያደርጋቸው ብቸኛው ጉዳይ ነው። ቡድኑ በተከታታይ ሳምንታት ከተጋጣሚው የተሻለ እንቅስቃሴ አድርጎ የግብ ዕድሎች መፍጠሩ እንዲሁም ከስድስት ተከታታይ ጎል አልባ ጨዋታዎች ግቦችን ማስቆጠር መጀመሩ በጥሩነት የሚነሳለት ጉዳይ ቢሆንም በፊት መስመር ላይ የሚታየው ህፀፅ የተሞላበት የውሳኔ አሰጣጥ ችግርና ለስህተቶች ተጋላጭ የሆነው የኋላው መስመር ከጨዋታዎች ውጤት ይዞ እንዳይወጣ እክል ሆኖበታል።

በነገው ጨዋታ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ያለውና እጅግ የተሻሻለው መቻል እንደመግጠሙ አንዳች ነገር ከጨዋታው ይዞ እንዳይወጣ ሊያደርገው ይችላል ተብሎ ቢገመትም ውስን ለውጦችና መሻሻሎች ቡድኑን ሌላ መልክ ሊሰጠው የሚችልበት ዕድልም ሰፊ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ላይ እየታየ የሚገኘው አንፃራዊ መሻሻል ወልቂጤ ከተማ ቀድሞ ነጥብ ከመጣሉ ጋር ተዳምሮ ቡድኑ በተለየ የሥነ-ልቦና ደረጃ ሆኖ ወደ ጨዋታው እንዲገባ ሊያደርገውም ስለሚችል ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆን እሙን ነው። ከነገው ወሳኝ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት ግን ከውጤትም በተጨማሪ ለቀጣይ ወሳኝ መርሀ-ግብሮችም ፋይዳው ትልቅ ነው።

በመቻል በኩል ግሩም ሐጎስ በቅጣት ምክንያት ጨዋታውን የሚያመልጠው ተጫዋች ሲሆን ሻሸመኔ ከተማዎች በቅጣት ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 4 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ መቻል 3 ጨዋታ ሲያሸንፍ አንዱን ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

የጣና ሞገዶቹ እና የጦና ንቦቹን የሚያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ምሽት ላይ ይከናወናል።

በመጨረሻው ሳምንት ሀምበሪቾን ሁለት ለባዶ ያሸነፉት ባህር ዳር ከተማዎች ላለፉት አስራ አንድ ጨዋታዎች ከሽንፈት ርቀዋል።

የጣና ሞገዶቹ በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ሳምንታት ያስመዘገቡት ደካማ ውጤት ጎተታቸው እንጂ በቅርብ ሳምንታት በተከታታይ ያስመዘገቡት ውጤት በዋንጫ ፉክክሩ ከዋነኞቹ ተዋናዮች አንዱ የሚያደርጋቸው ነበር። ስለ ባህር ዳር ከተማ መሻሻል ከተነሳ ዋነኛ ተወዳሽ የሚሆነው የመከላከል አደረጃጀቱ ነው። ቡድኑ ከሽንፈት ከራቀባቸው አስራ አንድ ጨዋታዎች ውስጥ በስምንቱ መረቡን ሳያስደፍር ከመውጣቱም ባሻገር የተመዘገቡበት ግቦች ሦስት ብቻ ናቸው።

ጠጣር የተከላካይ ጥምረት በመገንባት ቡድኑን ያሻሻሉት አሰልጣኝ ደግአረግ በፊት መስመር ተጫዋቾች የገጠማቸው ተደጋጋሚ ጉዳቶችና ቅጣቶች ለአማራጭ እጥረት እንደዳረጋቸው ይታመናል። ቡድኑ ሀምበሪቾን በገጠመበት የመጨረሻ ጨዋታ በርካታ የግብ ዕድሎች ፈጥሮ ሁለት ግቦችን ማስቆጠሩ በጥሩነት የሚነሳ ጉዳይ ቢሆንም ቀጣይነት ያለው ብቃት ማሳየትና ውስን የአፈፃፀም ክፍተቶች ማሻሻል ቀዳሚ ስራው መሆን ይጠበቅበታል።

በነገው ጨዋታ ቢያንስ አንድ ነጥብ ካሳኩ በሂሳባዊ ስሌት በሊጉ መቆየታቸው የሚያረጋግጡት ወላይታ ድቻዎች በሁለተኛው ዙር ያስመዘገቡት ደካማ ውጤት በጥሩ መንገድ የጀመረው የውድድር ዓመታቸው ሌላ መልክ አላብሶታል። ውጤት ከተስፋ ሰጪ ጥሩ የጨዋታ መንገድ ጋር አጣምሮ ጥሩ አጀማመር ማድረግ ችሎ የነበረው ቡድኑ የመጀመርያውን ዙር በሀያ ሁለት ነጥቦች በ8ኛ ደረጃነት ማጠናቀቅ ቢችልም በሁለተኛው ዙር ስድስት ነጥቦች ብቻ በመሰብሰብ በደካም ወቅታዊ አቋም ላይ ይገኛል።

የጦና ንቦቹ ሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች ከማስመዝገባቸው በተጨማሪ በጨዋታዎቹ ዘጠኝ ግቦች አስተናግደዋል፤ ከቡድኑ እንቅስቃሴ ባሻገር ቁጥሮችም እንደሚገልፁት ቡድኑ ጉልህ የመከላከል ክፍተቶች ተስተውሎበታል። በተለይም በንግድ ባንክ አምስት ለባዶ በተሸነፉበት ጨዋታ ላይ የተከተሉት የተጋጣሚን አቀራረብ ያላገናዘበ የጨዋታ ዕቅድ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በጨዋታው የተከላካይ መስመራቸውን ወደ ፊት ይበልጥ አስጠግተው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም ሰፊውን ክፍተት ለመሸፈን የነበራቸው ደካማ የመከላከል አቅም ተጋላጭ አድርጓቸዋል፤ በጨዋታው የተቆጠሩባቸው አራት ግቦችም የተጠቀሰውን ክፍተት ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ የተከላካይ ክፍሉን ማሻሻል ቀዳሚ ስራቸው ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የግብ ዕድሎች ፈጠራ ላይ የተዳከመው አጨዋወታቸውንም መፍትሔ የሚሻ ሌላው ጉዳይ ነው።

በባህር ዳር ከተማ በኩል አንበሉ ያሬድ ባዬህ በጉዳት ምክንያት የማይኖር ሲሆን ቸርነት ጉግሳ እና ፍሬው ሰለሞን ግን በነገው ጨዋታ ወደ ሜዳ እንደሚመለሱ ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ ዘጠኝ ጊዜ ተገናኝተው (የተሰረዘውን የ2012 ውድድር ዘመን አይጨምርም) ባህርዳር ከተማ 3፣ ወላይታ ድቻ አንድ ጊዜ አሸንፈው 5 ግንኙነታቸው በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የጣና ሞገዶቹ 7፣ የጦና ንቦቹ በበኩላቸው 5 ጎሎችን አስቆጥረዋል።