በ14ኛው ሳምንት የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች አናት ላይ የተቀመጡት ንግድ ባንክ እና ሀዋሳ ያለ ጎል አቻ ሲለያዩ ኤሌክትሪክ እና ሲዳማ ቡና ድል አስመዝግበዋል።
በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ከመመራት ተነስተው ከዕረፍት በኋላ በተቆጠሩ ጎሎች 2-1 አሸንፈው ወጥተዋል።
በመጀመሪያ አጋማሽ አዲስ አበባ ከተማዎች የተሻለ የበላይነት የነበራቸው ሲሆን በ32ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ፊት የሄደውን ኳስ ዳግማዊት ሰለሞን ወደ ግብነት ለውጣ ቡድኗን መሪ አድርጋ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ተሻሽለው የተመለሱት ሲዳማ ቡናዎች አከታትለው ባስቆጠሯቸው ጎሎች ሦስት ነጥብ አሳክተዋል። 54ኛው ደቂቃ ላይ ፊርማዬ ከበደ ከመስመር የመታችው ኳስ ከመረብ አርፎ ቡድኗን አቻ ስታደርግ በድጋሚ ፊርማዬ 69ኛው ደቂቃ ላይ ከተመሳሳይ ቦታ በመምታት ጎል አስቆጥራ ሲዳማን የ2-1 አሸናፊ ማድረግ ችላለች።
በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ኤሌክትሪክ በግብ ተንበሽብሾ ሀምበርቾን 4-0 አሸንፏል።
ኤሌክትሪኮች የበላይነታቸው በተስተዋለበት የመጀመሪያ አጋማሽ በርካታ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉ ሲሆን 27ኛው ደቂቃ ላይ እታለም አመኑ ከርቀት ወደ ግብ የላከችው ኳስ የሀምበርቾ ግብ ጠባቂ የአቋቋም ስህተት ታክሎበት ኤሌክትሪን ቀዳሚ ያደረገች ጎል አስቆጥራለች።
ከዕረፍት መልስ ኤሌክትሪኮች ይበልጥ አይለው የመጡ ሲሆን በአንፃሩ ሀምበርቾዎች መረጋጋት ተስኗቸው ምላሽ መስጠት ሳይችሉ ቀርተዋል። በዚህም 50ኛው ደቂቃ ላይ ሽታዬ ሲሳይ ወደ ውስጥ ይዛ በመግባት አስቆጥራ መሪነቱን ወደ ሁለት ስታሰፋ 52ኛው ደቂቃ ላዬ ሲሳይ ገብረዋህድ ከመስመር የተቀበለችውን ኳስ ከርቀት በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥራለች። በ67ኛው ደቂቃ ደግሞ ተቀይራ የገባችው ሳራ ነብሶ ከርቀት ግሩም ግብ አስቆጥራ ጨዋታው በኤሌክትሪክ 4-0 አሸናፊነት ተፈፅሟል።
የሳምንቱ የመጨረሻ እና ተጠባቂ ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር አስተናግዶ ያለ ጎል ተጠናቋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ባንኮች በተደጋጋሚ የተቃራኒ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የሀዋሳዎች ጥሩ መከላከል ከጎል እንዳይገናኙ አድርጓቸዋል። 36ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ መትታ ግብ ጠባቂዋ ቤተልሔም ያዳነችባትም የምትጠቀስ ሙከራ ነበረች።
ተመሳሳይ ሂደት በነበረው ሁለተኛ አጋማሽ ንግድ ባንኮች የተሻለ የጎል ዕድል የፈጠሩ ሲሆን 78ኛው ደቂቃ ላይ አርያት የተሻረገላትን ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ብታስቆጥርም በእጅ ነክታለች በሚል ሳይፀድቅ ቀርቷል።
የጨዋታው መገባደጃ 88ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳዋ ሳራ ካዲዮ የዳኛ ውሳኔ በመቃወሟ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣችበት ሌላው የጨዋታው ክስተት የነበረ ሲሆን ባንክ ጎል ለማስቆጠር ጫና ፈጥሮ ቢጫወትም ሀዋሳዎች ግባቸውን ሳያስደፍሩ በመውጣት በአቻ የተጀመረው 14ኛ ሳምንት በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ ሆኗል።