ኢንስትራክተር አብርሃም በመጀመሪያው የኮሳፋ የቴክኒካል ጥናት ቡድን ሲምፖዚየም ተሳተፉ

ያለፉትን ሁለት ቀናት በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የኮሳፋ የቴክኒካል ጥናት ቡድን ሲምፖዚየም የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ተሳትፎ አድርገዋል።

በደቡባዊ የአህጉራችን ክፍል የሚገኙ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችን ያቀፈው የኮሳፋ ዞን ያለፉትን ሁለት ቀናት በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ሲምፖዚየም በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ አከናውኗል። በዚህ ሲምፖዚየም ላይ የአስራ አራቱም ሀገራት ቴክኒካል ዳይሬክተሮች፣ የወንድ እና የሴት ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች እና ዋና ፀሀፊዎች ተገኝተዋል። የሀገራችን ሰው የሆኑት የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር እና የፊፋ ቴክኒካል ኤክስፐርት አብርሃም መብራቱም በሁለቱ ቀን ሲምፖዚየን ተካፍለዋል።

በዋናነት በሲምፖዚየሙ ስለፐርፎርማንስ ትንተና አስፈላጊነት፣ ስለሪከቨሪ እና ሪሀቢሊቴሽን እንዲሁም ስለስፖርት ሳይንስ የእግርኳስ ጥቅም ሰፊ ውይይት ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪም የስፖርት ሳይኮሎጂ ለአሠልጣኞች ስለሚሰጠው ጥቅም ሀሳቦች ተነስተው ኢንስትራክተር አብርሃም የነበሩበት የአይቮሪኮስት የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የኮሳፋ ሀገራት ስለነበራቸው አቋም በቴክኒካል ጥናት ቡድኑ ገለፃ ተደርጓል። በመጨረሻም ኢንስትራክተር አብርሃምም የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተሮችን እና TSG ፓናልን ወክለው የመዝጊያ ንግግር አድርገው ሲምፖዚየሙ ተገባዷል።