ሪፖርት| ኢትዮጵያ ቡና ሀምበሪቾን ረምርሟል

በውድድሩ ዓመቱ ብዙ ግቦች የተቆጠረበት ጨዋታ በቡናማዎቹ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ሻሸመኔን ካሸነፈው ቋሚ አሰላለፍ መስፍን ታፈሰና ብሩክ በየነ በአንተነህ ተፈራና አማኑኤል አድማሱ ተክተው ሲገቡ ሙሉ ስብስባቸውን ይዘው ያልቀረቡት ሀምበሪቾዎች በበኩላቸው በባህርዳር ከተማ ሽንፈት ከገጠመው ቡድን ፓሉማ ፓጁና በሃይሉ ተሻገር በምንታምር መለስና ዘሩባቤል ፈለቀ ትክተዋል።

ሁለቱም ቡድኖች ባደረጉት ተመጣጣኝ የሚባል ፉክክር የጀመረው ጨዋታው ጅማሮው በሙከራዎች ያልታጀበና ንፁህ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። በመጀመርያ ደቂቃዎች ቡናማዎቹ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርጉም ብልጫቸው ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች አልዘለቀም። በአስራ ስድስተኛው ደቂቃ ግን ሙና በቀለ ከግቡ አፋፍ ኳስ በእጁ በመንካቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ ኢትዮጵያ ቡናዎችም ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል፤ አማኑኤል ዮሐንስ የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብነት ቀይሮም ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

በጎዶሎ ተጫዋች ጨዋታውን ለመቀጠል የተገደዱት ሀምበሪቾዎች የተጫዋቾች ሽግብር በማድረግ እስከ መጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ድረስ ጥሩ በመንቀሳቀስ ጥቂት የማይባሉ ዒላማቸውን ያልጠበቁ የግብ ሙከራዎች አድርገዋል። የአንድ ተጫዋች ብልጫ ቢያገኙም የቁጥር ብልጫውን ተጠቅመው በሚጠበቀው ልክ ጨዋታውን መቆጣጠር ያልቻሉት ቡናማዎቹም በሰላሣ ሁለተኛው ደቂቃ በአማኑኤል አድማሱ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ልዩነቱ ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል። አጥቂው አስራት ቱንጆ ከቀኝ መስመር አሻግሯት በተከላካዮች የተግቦት ችግር ከመሐመድኑር ናስር የተሻገረችለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ሞከሯት ግብ ጠባቂው በአግባቡ ሳይቆጣጠራት ከቀረ በኋላ ከመረብ ጋር አዋህዷታል።

ከመጀመርያው አጋማሽ በተለየ በኢትዮጵያ ቡና ፍፁም ብልጫ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ ቡናማዎቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱበት ነበር። ይህንን ተከትሎም አጋማሹ በተጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች በመሐመድኑር ናስር ለግብ የቀረበ ሙከራ ካደረጉ በኋላ ልዩነቱን ወደ ሦስት ግቦች ከፍ የሚያደርጉበት ግብ አግኝተዋል። አማኑኤል በግራ መስመር በኩል አፈትልኮ ከገባ በኋላ ወደ ሳጥን ያሻገራትን ኳስ አንተነህ ተፈራ መቷት ቋሚውን ለትማ ከተመለሰች በኋላ ግብ ጠባቂው ምንታምር መለስ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯታል።

ከግቡ በኃላም ብልጫውን ለማስቀጠል ከባድ ፈተና ያገጠማቸው ቡናማዎቹ በደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ወደ ሙከራነት ያልተቀየሩ ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች ካባከኑ በኋላ ግብ አስቆጥረዋል። አማኑኤል በጥሩ መንገድ ወደ ሳጥን ይዟት በመግባት መቷት ግብ ጠባቂው ሲመልሳት ከግቡ አጠገብ የነበረው መሐመድ ኑር ናስር ከመረብ ጋር አዋህዶ የግብ መጠኑን አራት አድርሷል።

በአጋማሹ የመጀመርያቸው በሆነችና በፍቃዱ አስረሳኸኝ ባደረጋት ሙከራ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል የደረሱት ሀምበሪቾዎች ከሙከራው ጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። አላዛር አድማሱ ከአብዱልከሪም ዱግዋ የተሻገረችለትን ኳስ ተረጋግቶ በማስቆጠር ቡድኑ ከአራት ጨዋታዎች ጥበቃ በኋላ ከግብ ጋር አስታርቋል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ቡናማዎቹ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት በጫላ ተሺታና መሐመድኑር ናስር አማካኝነት ሁለት ግቦች አስቆጥረው በጨዋታው ያስቆጠሩት የግብ መጠን ስድስት አድርሰዋል።
ጫላ ተሺታ በግል ጥረቱ ተጫዋቾች አልፎ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ ስያስቆጥር መሐመድኑር ናስር አስራት ቱንጆ ከመስመር ወደ ሳጥኑ ያሻገራትን ኳስ ተረጋግቶ በማስቆጠር ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ ስድስተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀው በኋላ ሀሳባቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ብሩክ ሲሳይ በውጤቱ በጣም ማዘናቸውን ገልፀው ቀይ ካርዱ የጨዋታ እቅዳቸውን እንዳበላሸው ተናግረዋል። አሰልጣኙ አክለውም በብዙ ነገሮች እንደተቸገሩ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በበኩላቸው ጨዋታው ጥሩ እንደነበር ጠቅሰው ጨዋታው ባሰቡት ልክ እንደሄደ ተናግረዋል፤ ከዚ በተጨማሪ ከዚ በፊት በግብ አከባቢ የነበሩ ጥድፍያዎች እንደቀነሱም ገልፀዋል።