ሪፖርት | ኃይቆቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ሊጉ ከመቋረጡ አስቀድሞ የተካሄደው የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን ባለድል አድርጎ ተገባዷል።

ሀድያ ሆሳዕና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ከወጣበት ቡድኑ ግርማ በቀለ፣ እንዳለ አባይነህ፣ ደስታ ዋሚሾ እና ፀጋዓብ ግዛው በማሳረፍ ብሩክ ማርቆስ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ እና ዳዋ ሆጤሳን ወደ ስብስባቸው ሲቀላቅሉ። ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በመቻል ከደረሰበት አሳዛኝ ሽንፈት በኋላ ግብጠባቂውን ቻርልስ ሉካጎ፣ ፀጋብ ዮሐንስ፣ እኔው ካሳሁን እና አቤኔዘር ዮሐንስን አስቀምጠው ግብጠባቂ ፅዮን መርድ፣ በረከት ሳሙኤል፣ ታፈሰ ሰለሞን እና ሲሳይ ጋቸ ተክተው ይዘው ለጨዋታው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ፌደራል ዳኛ ሙሉቀን ያረጋል በመሩት የሳምንቱ የመጨረሻ የምሽት ጨዋታ ፈጣን የጎል ሙከራ በማድረግ ነበር ጅማሮውን ያደረገው። ነብሮቹ በ3ኛው ደቂቃ ከመማዕዘን ተደርቦ የተመለሰውን ራሱ ሳሙኤል ዮሐንስ በድጋሚ ያሻማውን ተመስገን ብርሃኑ ከጎሉ ፊት ለፊት በግንባር ቢመታም ግብጠባቂው ፅዮን መርዕድ በቀላሉ ኳሱን ተቆጣጥሮታል።

የምሽቱ ጨዋታው ሞቅ ባለ እንቅስቃሴ ቀጥሎ በ11ኘው ደቂቃ ጎል ልንመለከት ችሏል። ከአማኑኤል ጎበና የተነሳው የየሀዋሳ ከተማ የመልሶ ማጥቃት አጨዋት በግራ መስመር እዮብ አለማየሁ ኳሱን ተቆጣጥሮ ወደ ፊት በመግፋት በድንቅ ሁኔታ ያሻገረውን ኳስ ነፃ ሆኖ ያገኘውን እስራኤል እሸቱ በግንባር በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከአንድ ደቂቃ በኋላ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ወደ ማጥቃት ሽግግር የገቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ቴዎድሮስ ታፈሰ አሾልኮ የላከውን ዳዋ ሆጤሳ ነፃ ኳስ ሳጥን ውአግኝቶ ከመረቡ ጋር አገናኘው ሲባል ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረው ለቡድኑ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ነበር። ኃይቆቹ ተጋጣሚያቸው ኳሱን ተረጋግተው እንዳይጫወቱ ተጭነው በመጫወት 23ኛው ደቂቃ የሀድያው ግብጠባቂ ያሬድ በቀለ በቅብብሎች መሐል የፈጠረውን ስህተት ተከትሎ ዓሊ ሱሌማን እግሩ የገባውን ኳስ ቦታ አይቶ ቢመታውም ግብጠባቂው ያሬድ ስህተቱን በማረም ጎል እንዳይሆን አድርጎታል።

በሁለቱም ቡድን በኩል ባልተረጋጋ ሁኔታ በሚደረጉ የኳስ ንኪኪዎች እና ወደ ፊት የሚጥሏቸው ረጃጅም ኳሶቻቸው ጥራት ይጎላቸው የነበረ በመሆኑ በጨዋታው ጅማሬ ያስመለከቱንን ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ መቀዛቀዝ አምርቶ ሙከራዎችን እንዳንመለከት አድርጎታል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ በ51ኛው ደቂቃ ሀድያዎች ወደ ጨዋታው የገቡበትን ጎል አግኝተዋል። ተመስገን ብርሀኑ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ከሳጥኑ ውጭ የግራ መስመር በኩል የተሰጠውን ቅጣት ምት ዳዋ ሆጤሳ በድንቅ ሁኔታ ወደ ጎልነት ቀይሮት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። በማጥቃቱ በኩል ተሻሽለው የቀረቡት ቡድኖቹ ተደጋጋሚ ሳጥን ውስጥ በመድረስ ጎሎች ፍለጋ የሚያደርጉት ጥረት የጨዋታውን እንቅስቃሴ ከፍ ወደ አለ ግለት ቀይሮታል።

በዚህም ሂደት የቀጠለው ጨዋታ 68ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር መነሻ ያደረገው ኳስ ዓሊ ሱሌማን ወደ ጎል ሲመታው ከድር ኩሊባሊ ኳስ በእጅ በመንካቱ ፌደራል ዳኛ ሙሉቀን የተሰጡትን ፍፁም ቅጣት ምት እራሱ ዓሊ ወደ ጎልነት በመቀይር ኃይቆቹን መሪ አድርጓል። ድንቅ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ኤርትራዊው አጥቂ ዓሊ ሱሌማን በሊጉ ያስቆጠራቸውን የጎሎች መጠን ወደ አስራ ስድስት ከፍ ማድረግ ችሏል።

የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ኃይል የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ ሆኖ ሲቀጥል። ሀዋሳዎች መሪ ከሆኑ በኋላ የጥንቃቄ አጨዋወት በመምረጥ ውጤቱን ለማስጠበቅ ባለመ መልኩ በመልሶ ማጥቃት ጥቃት ለመሰንዘር ሲያስቡ በአንፃሩ ነብሮቹ በሙሉ አቅማቸው ለማጥቃት ያደረጉት ጥረት 88ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆጤሳ ከሳጥን ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ ቢመታውም ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ለነብሮቹ የሚያስቆጭ ለሀዋሳዎች እፎይታ የሚሰጥ አጋጣሚ ነበር።

በተጨማሪ ደቂቃዎች ተቀይሮ የገባው ፀጋአብ ዮሐንስ ተመስገን ብርሀኑ ላይ በሰራው አደገኛ ጥፋት ተከትሎ በሁለት ቢጫ በቀይ ካር ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጎ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 2-1 አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ ሆኗል።

ወደ አሸናፊነት የተመለሱት አሰልጣኝ ዘራይ ሙሉ በአስተያየታቸው ጠንካራ ቡድን እንደገጠማቸው እና ከዕረፍት በፊት ጫና ፈጥረው እንደተጫወቱ ተናግረው ስኬታማ የሆነው የተጫዋቾች ቅያሪ የሚፈልጉትን ውጤት እንዲያገኙ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል። ተሸናፊው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በቡናቸው ባልተረጋጋ ሁኔታ ጎል እንደተስተናገደባቸው ገልፀው የሀዋሳ ታክቲካሊ ዲሲፒሊን መሆናቸው እና የሀይል አጨዋወት በተለይ ተከላካይ ክፍላቸው እንዳይረጋጋ በመሆኑ በጨዋታው ስኬታማ እንዳይሆኑ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።