ጊኒ ቢሳው አሁንም ለተጨማሪ ተጫዋቾች ጥሪ አቅርባለች

የፊታችን ሀሙስ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያለባት ጊኒ ለተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጓ ተሰምቷል።

በ2026 ለሚደረገው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተከናወኑ ሲሆን የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታዎችም በዚህ ሳምንት በተለያዩ ሀገራት ይደረጋሉ። በምድብ አንድ ከሀገራችን ኢትዮጵያ ጋር የተደለደለችው ጊኒ ቢሳው ከዋልያዎቹ እና ፈርዖኦቹ ጋር በተከታታይ ላለባት ጨዋታ ዝግጅቷን እያደረገች ትገኛለች።

በአሠልጣኝ ልዊስ ቦዋ ሞርት የሚመራው ቡድኑ ከትናንት በስትያ ያለ ልምምድ ዕረፍት ካደረገ በኋላ በትናንትናው ዕለት ወደ ልምምድ ሲመለስ አዳዲስ ተጫዋቾችን ይዞ እንደነበረ ተመላክቷል። በዚህም በሀገሪቱ ሊግ ከሚሳተፈው ስፖርቲንግ ሲ ጂ ቢ ፉስካኖ እንዲሁም ከአንጎላ ሊግ ሴኔ ካማራ አዲስ ጥሪ እንደደረሳቸው ታውቋል።