በቅርቡ በዩዲኔዜ ዋናው ቡድን የመጀመርያ ጨዋታው ያከናወነው ተስፈኛ

ከወዲሁ ከዴስቲኒ ኡዶጊ ጋር እየተነፃፀረ የሚገኘው ትውልደ ኢትዮጵያዊ

እንድሪስ ስካራሜሊ በዩዲኔዜ ወጣት ቡድን ውስጥ ብቅ ያለ አዲስ ባለ ተሰጥኦ መሆኑን በግልፅ እያሳየ ነው። በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ቡድን በቀጥታ ወደ ከአስራ ዘጠኝ ዓመት በታች ቡድን በማደግ በሀያ ሦስት ጨዋታዎች መሳተፍ የቻለው ይህ የቀኝ መስመር ተከላካይ በያዝነው ዓመት አራት ግቦች ሲያስቆጥር አንድ ግብ የሆነች ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።


በሚወዳደርበት Primavera 2 – A ለወደፊቱ ትልቅ ደረጃ ላይ ይደርሳሉ ተብለው ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች ተርታ የሚመደበው ይህ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከወራት በፊት የዩዲኔዜ ዋናው ቡድን ከ ፓዶቫ ጋር ባደረገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ ላይ ለዋናው ቡድን የመጀመርያ ጨዋታውን አድርጓል።  እንድሪስ ሙሉ ለሙሉ ወደ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋችነት ከመግባቱ በፊት ለአምስት ዓመታት ያህል በአትሌቲክስ ተሳትፎ አድርጓል። ከዕድሜ እኩዮቹ አንፃር ሲታይ ግዙፍ የሆነው ተክለ ሰውነቱ፣ ፍጥነቱ፣ የመከላከል እና የማጥቃት ችሎታው እንዲሁም በዘንድሮ የውድድር ዓመት ያዳበረው ጎል የማስቆጠር ብቃቱም የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።


ገና በአሥራ ሰባት ዓመቱ አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ እየተጫወተ የሚገኘው ይህ ተጫዋች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የጨዋታዎች ብዛት እና ተሳትፎው ወደፊት ተስፋ ሰጪ የእግር ኳስ ኮከብ የመሆን አቅም እንዳለው እያሳየ ነው። ተክለ ሰውነቱ እና ፍጥነቱም በብዙዎች ዘንድ ከቀድሞ የዩዲኔዜ እና የአሁኑ የስፐርስ ተጫዋች ዴስቲኒ ኡዶጊ ጋር እየተነፃፀረ ሲገኝ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በዋናው ቡድን ደረጃ ነጭና ጥቁር ማልያ ለመልበስ የሚያበቃ ብቃት በማሳየት ላይ ይገኛል፤ በጥሩ እድገት የሚገኘው ብቃቱን ካዳበረ በቀጣይ ዓመታት በትልቅ ደረጃ የመጫወት አቅም አለው።