የነገውን የዋልያዎቹ ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች ታውቀዋል

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ እና ማላዊን ጨዋታ የመሩት አልቢትር ከሦስት የሀገራቸው ረዳቶች ጋር በመሆን ዳግም ነገ የሚደረገውን የኢትዮጵያ ጨዋታ እንዲመሩ ተመድበዋል።

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ሦስተኛ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚደረጉ ሲሆን በምድብ አንድ የምትገኘው ሀገራችን ኢትዮጵያም ነገ ምሽት 1 ሰዓት በቢሳው ከተማ ስታዲዮ 24 ሴቴምብሮ ከጊኒ ቢሳው ጋር ወሳኝ ጨዋታዋን ታከናውናለች።

ይህንን ወሳኝ ጨዋታም አራት ቢኒናዊ አልቢትሮች እንደሚመሩት መመደባቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። በዚህም ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ጂንዶ ሉዊስ ሆንግናንዳንዴ ሲመሩት ኤሪክ አልሪች እና ኮርቴል ጆ በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ኢሳ ሙሐመድ በአራተኛ ዳኝነት ተሳትፎ እንዲያደርጉ በካፍ ምደባ ደርሷቸው ቢሳው ከተማ ገብተዋል።

የጨዋታው የመሐል ዳኛ ጂንዶ ሉዊስ ሆንግናንዳንዴ እና ረዳቱ ኤሪክ አልሪች ከወራት በፊት ሰኔ 13 2015 የተደረገውን የኢትዮጵያ እና ማላዊ ጨዋታ መርተው ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ያለ ጎል አቻ መለያየታቸው ይታወሳል።