ሪፖርት | አራት ጎሎች የተቆጠሩበት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

የ28ኛ ሳምንት የመጀመርያ ቀን የምሽት ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ እና በወልቂጤ ከተማ መካከል ተካሂዶ አስገራሚ ክስተቶች ተስተናግደውበት በአቻ ውጤት ተገባዷል።

ሀዋሳ ከተማ ከአስከፊው የአዳማ ከተማ አምስት ለዜሮ ሽንፈት በኋላ የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። መድሀኔ ብርሀኔ፣ እንየው ካሳሁን እና ታፈሰ ሰለሞንን በማሳረፍ በምትኩ ሰለሞን ወዴሳ፣ ሲሳይ ጋቾ እና አብዱልባሲጥ ከማልን ይዘው ገብተዋል። ወልቂጤ ከተማም ከከባዱ የኢትዮጵያ ቡና አራት ለዜሮ ሽንፈት ማግስት ከሜዳ ውጭ ባለው ችግር ምክንያት ያጧቸውን ስድስት ተጫዋቾችን በመቀየር አስገብተዋል። በዚህም ግብ ጠባቂ ናትናኤል ጃምቦ፣ ወንድማገኝ ማዕረግ፣ አድናን ፋይሰል፣ በቃሉ ገናናው፣ ቤቢ ታደለ፣ ጀይላን ከማል እና ፉአድ አብደላን አሳርፈው ግብጠባቂ ፋሪስ አለዊ፣ አዳነ በላይነህ፣ ጌቱ ኃይለማርያም፣ ተስፋዬ መላኩ፣ ዳንኤል ደምሴ፣ ሙሉዓለም መስፍን እና ተመስገን በጅሮንድን በመተካት ለጨዋታው ዝግጁ ሆነዋል።

የ28ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን የምሽት ጨዋታን ፌዴራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ አስጀምረውታል። ቀዝቀዝ ብሎ ጅማሬውን ባደረገው የምሽቱ ጨዋታ ሀይቆቹ ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ወደ ፊት ለመሄድ ያሰቡ ቢመስልም ብዙም ውጤታማ አልነበሩም። በአንፃሩ በሠራተኞቹ በኩል የማጥቃት ፍላጎት ቢታይም ዋና ትኩረታቸውን መከላከል ላይ አድርገው አልፎ አልፎ ወደ አደገኛው ዞን ቢገቡም ጥራት ያላቸው ኳሶች በማቅረብ በኩል የነበራቸው ውስንንት ዕድሎችን እንዳይፈጥሩ አድርጎባቸዋል።

በአጠቃላይ የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጠር በሁለቱም ቡድኖች በኩል የታየው እንቅስቃሴ ወደ አሰልቺነት ቢለወጥም በ32ኛው ደቂቃ ጎል ሊያስመለክተን ችሏል። ካልተጠበቀ አቅጣጫ የሀዋሳው አማካይ አብዱልባሲጥ ከማል ከርቀት በቀጥታ ወደ ጎል በመምታት የቡድኑን ቀዳሚ ጎል አስገኝቷል። ዘለግ ላለ ደቂቃ የጎል ሙከራዎች ሳይታዩበት ቆይቶ ጎሉ ከተቆጠረ በኋላ የጨዋታው እንቅስቃሴ ህይወት ይኖረዋል ተብሎ ቢታሰብም በሁለቱም በኩል የኳስ ንክኪዎቻቸው ትርጉም አልባ ሆኖ አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ የጀመረው ጨዋታ በ47ኛው ደቂቃ ወልቂጤዎችን በፍጥነት ወደ ጨዋታው የመለሰ ፍፁም ቅጣት ምት አስገኝቷል። ጋዲሳ መብራቴ ላይ በረከት ሳሙኤል የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከመጀመሪያው አጋማሽ በተቃራኒ ጥሩ ወደ ጎል የሚደርሱ ምልልሶችን ባስመለከተን ሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳዎች አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችላቸውን ጥቃት በ51ኛው ደቂቃ በዓሊ ሱሌይማን አማካኝነት ቢሰነዝሩም የግቡ ቋሚ ከልክሏቸዋል።

56ኛው ደቂቃ ላይ በወልቂጤዎች በኩል ከተሻጋሪ ኳስ ሙሉዓለም መስፍን ላይ ግልፅ ጥፋት ቢፈፀምበትም የዕለቱ ዳኛ እያሱ ፈንቴ በዝምታ ማለፋቸው ሠራተኞቹን አላስደሰታቸውም። ጨዋታው ወደ ተለያዩ ውዝግቦች እና ማራኪ ፉክክሮች ቀጥሎ ሀዋሳ ከተማዎች በ64ኛው ደቂቃ ዓሊ ሱሌማን ላይ ዉሀቡ አዳምስ ጥፋት ሰርቷል በማለት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ተጠቅሞ ራሱ ዓሊ ሱሌይማን ቡድኑን መሪ ያደረገች ሁለተኛ ጎል አስገኝቷል።

ከጨዋታው እንቅስቃሴ ይልቅ በዳኝነት ውሳኔ ላይ በሚቀርቡ ቅሬታዎች ታጅቦ የቀጠለው ጨዋታ ሀዋሳዎች ያስቆጠሩትን የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ተገቢ አይደለም ብለው ወልቂጤዎች ተቃውመው አቅርበው ሳይጨርሱ በተቃራኒው ሀዋሳዎች ዓሊ ሱሌይማን ላይ ፍፁም ቅጣት ምት የሚያሰጥ ጥፋት ተከስቶ ዳኛው በዝምታ ማለፋቸው ተገቢ አይደለም በማለት በተመሳሳይ ቅሬታ ማሰማታቸው አስገራሚ ክስተት ነበር። ከተከታታይ ሁለት የፍፁም ቅጣት ጎሎች በኋላ የጨዋታው እንቅስቃሴ ቀጥሎ በ82ኛው ደቂቃ ወልቂጤዎች በድጋሚ ወደ ጨዋታው የገቡበትን ግሩም የቅጣት ምት ጎል ጋዲሳ መብራቴ ለቡድኑም ለራሱም ሁለተኛ የአቻነት ጎል አስቆጥሯል። በቀሩት ደቂቃዎች ብዙም የተለየ ነገር ሳንመለከት ጨዋታው በሁለት አቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ ሆኗል።


ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወልቂጤው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት በሰጡት አስተያየት ጥብቅ ያለ ጨዋታ ቢሆንም ከዕረፍት መልስ የጨዋታ መንገዳቸውን ቀይረው መግባታቸው አንድ ነጥብ እንዲያገኙ እንደረዳቸው ገልፀው በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች በሊጉ ለመቆየት በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ትልቅ ተጋድሎ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። የሀዋሳው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው የወልቂጤ አጨዋወት ሁኔታ ብዙ ቦታ እንዳያገኙ እንዳደረጋቸው ገልፀው የተቆጠረባቸው ሁለተኛ ጎል በተከላካዮቻቸው እና በግብጠባቂያቸው የአቋቋም ችግር በመሆኑ ሁለቱም ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ብለዋል።