መረጃዎች| 113ኛ የጨዋታ ቀን

የ28ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ነገም ቀጥለው ይካሄዳሉ፤ በዋንጫ ፉክክሩ ትልቅ ትርጉም ያለውን ጨዋታ ጨምሮ ጎሎች እያዘነቡ እዚህ የደረሱት ቡድኖችን የሚያገናኘውን ጨዋታ አስመልክተን ያዘጋጀናቸው መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ኢትዮጵያ ቡና

በርካታ ግቦች እያስቆጠሩ ተከታታይ ድሎች ያስመዘገቡ ሁለት ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ ማራኪ ፉክክርና በርከት ያሉ ግቦች ይቆጠሩበታል ተብሎ ይጠበቃል። በእንቅስቃሴ ጥሩ ፉክክር እንደሚያስመለክተን በሚጠበቀው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን በሰንጠረዡ አጋማሽ ካለው የነጥብ መቀራረብ ከፍ ለማለት ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከተከታዮቹ ርቆ የ3ኛ ደረጃነቱን ለማስጠበቅ ጨዋታው እስፈላጊያቸው ይሆናል።

ሰባት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ የተመነደጉት መድኖች የአሸናፊነታቸው መንገድ ለማስቀጠል ከኢትዮጵያ ቡና ይፋለማሉ። ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረግ ፈጣን ሽግግሮች የተጋጣሚን የግብ ክልል መጎብኘት የሚያዘወትረው ቡድኑ ነገም እንደ ወትሮ በተመሳሳይ አቀራረብና የጨዋታ መንፈስ የሚቀርብ ከሆነ ለተጋጣሚው ቡድን አደጋ ነው። መድን ላቅ ያለው የአፈፃፀም ብቃቱ ይዞ ከመዝለቁም በተጨማሪ በፊት መስመር ያለውን የግብ ምንጭ አስፍቷል፤ ቡድኑ የፊት መስመር ጥምረት ጥንካሬውን ማስቀጠሉ እንደ አወንታ የሚነሳለት ጉዳይ ቢሆንም ከዚህ ቀደም ለስህተቶች ተጋላጭ የነበረው የቡና የመከላከል አደረጃጀት ጉልህ ስህተቶች እየቀነሰ መምጣቱ ግን እንደከዚህ ቀደም በርከት ያሉ ግቦች ለማስቆጠር ፈታኝ ያደርግለታል ተብሎ ይገመታል።

ኢትዮጵያ ቡና ሀምበርቾና ወልቂጤ ከተማ ላይ አስር ግቦች አስቆጥሮ ከረታ በኋላ ለነገው ጨዋታ ይደርሳል። ቡና ደካማ የተጋጣሚ የመከላከል አደረጃጀት ወይንም ለፈጣን ጥቃቶች የተመቸ ተጋላጭ የሆነ ቡድኑ ካገኘ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር እንዲሁም ለውጤት ማብቃት እንደሚችል ባለፉት ጨዋታዎች ደጋግሞ አሳይቶናል። ተጋጣሚያቸው መድን ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የመከላከል መዋቅር የገነባ ቡድን ቢሆንም የኢትዮጵያ ቡና ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወትም ቀላል ፈተና እንደማይሆን የታወቀ ነው። ቡናማዎቹ በኩል በጨዋታው ትልቁ የቤት ስራ ሊሆን የሚገባው የኋላ ክፍላቸው ጉዳይ ነው፤ እርግጥ የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት መሻሻሎች አሳይቷል በነገው ዕለትም ባለፉት ጊዜያት በአደረጃጀት እና በግለሰባዊ ስህተቶች ሲከፈት የሚታየው የተከላካይ መስመሩን ይበልጥ አጠናክሮ መቅረብ ወሳኝነት አለው።

በሌላው የሜዳ ክፍሎች ከሚኖረው ፉክክር በተጨማሪ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ያለው ውጤታማው የፊት ጥምረትና የኋላ ክፍሎቻቸው የሚያደርጉት ፍልምያም ጨዋታው አጓጊ ያደርገዋል።

በጨዋታው የኢትዮጵያ ቡናዎቹ ጫላ ተሺታ ፣ ሬድዋን ናስር እና መስፍን ታፈሰ በጉዳት ምክንያት አይኖሩም። በኢትዮጵያ መድን በኩል አለን ካይዋ እና አብዲሳ ጀማል በተመሳሳይ በጉዳት የነገው ጨዋታ ያመልጣቸዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 28 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 12 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መድን 7 ጊዜ አሸንፏል ፤ 9 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና 46 ጎሎች ሲያስቆጥር ኢትዮጵያ መድን 31 ጎሎች አስቆጥሯል።

ሲዳማ ቡና ከ መቻል

ሲዳማ ቡና ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ መቻል በበኩሉ አሸንፎ ቀድሞ የነጥብ ልዩነቱን በማጥበብ መሪው ላይ ጫና ለማሳደር የሚያደርጉት የዋንጫ ፉክክሩ ሁኔታ የሚወስን ተጠባቂ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል

ሀምበሪቾን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ከተከታታይ ሽንፈቶች ያገገሙት ሲዳማ ቡናዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባከናወኑት ጨዋታ የታየቸው ዕድሎች የመጠቀም ጉልህ ክፍተት በውስን መልኩ ቀርፈዋል። ሆኖም ከዚህ ቀደም የወጥነት ችግር የነበረበትና ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ወደ ፊት በመድረሱ በኩል መሻሻል ያሳየው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ከመጨረሻው የሀምበሪቾ ጨዋታ አንፃር ነገ ከበድ ያለ ፈተና ይጠብቀዋል።

ቡድኑ ሁለቱ መስመሮችና የተጋጣሚው ጠንካራ ጎን የሆኑትና ከዚህ ቀደም የመቻልን ውጤታማነት ከፍ ያደረጉ የመሐል ለመሐል ጥቃቶች በመዝጋት ላይ ትኩረት ያደርጋል ተብሎ ሲጠበቅ ከጨዋታው ክብደት እንዲሁም የተጋጣሚ የአጨዋወት መንገድ ጥንቃቄ ላይ መሰረት ያደረገና በቶሎ ከራሱ ሜዳ በመልሶ ማጥቃት ለመውጣት የሚሞክር ዓይነት አቀራረብ ይዞ እንዲገባ ሊያስገድደውም ይችላል። በተጠቀሰው መንገድ የሚቀርብ ከሆነም በዋነኝነት አስተማማኝ የኋላ ክፍል ጥንካሬ ይዞ እንዲቀርብ ሊያግዘው ይችላል።

33 ነጥቦች ሰብስበው የመጀመርያውን ዙር በመሪነት ያጠናቀቁት መቻሎች ተከታታይ ሽንፈት አስተናግደው በጀመሩት ሁለተኛው ዙር በርከት ያሉ ነጥቦች ከስረዋል፤ ቡድኑ በመጨረሻዎቹ አምስት የሊግ ጨዋታዎች በብዙ መንገድ ተለውጦ ድንቅ እንቅስቃሴ ቢያደርግም በመሀል የከሰረው ሁለት ነጥብ በዋንጫ ፉክክሩ አንድ እርምጃ ወደ ኋላ እንዲቀር አስገድዶታል። መቻል ከመሪው በሦስት ነጥቦች ርቆ መገኘቱ ለዋንጫ ያለውን ተስፋ ንግድ ባንክ በሚገጥመው የነጥብ መንሸራተት የተንጠለጠለ ቢሆንም በፉክክሩ ለመግፋት በነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ይኖርበታል።

ቀደም ብለው በተከናወኑ አራት ጨዋታዎች አስር ግቦች ማስቆጠር ችሎ የነበረው መቻል በመጨረሻው መርሀ-ግብር የማጥቃት አማራጮቹ ቀንሰው ታይተዋል። እርግጥ ነው የነገው ጨዋታ ከተጋጣሚው የኋላ ክፍል አሁናዊ ሁኔታ አንፃር የተሻለ ክፍተት የሚያስገኝለት ቢሆንም በመጨረሻው መርሀ-ግብር 86′ ደቂቃዎች እንዲጠብቅ ያስገደደውና ከበርካታ ሳምንታት በኋላ ድጋሚ ያገረሸው ጉልህ የአፈፃፀም ክፍተትና በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ውስንነት መቅረፍ ይጠበቅበታል። በተለይም በተጫዋቾች ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ክፍተቶች ለሚመክኑ ዕድሎች ከወዲሁ መፍትሔ ማበጀት ግድ ይላል። መቻል ሦስት መርሀ-ግብሮች ብቻ በሚቀሩት ሊግ በሦስት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ለነገው ጨዋታ ደርሷል። በዋንጫ ፉክክሩ ያለውን ተስፋ ለመጠቀምም በተለየ ትኩረት ጨዋታውን እንደሚከውን ይጠበቃል።

ሁለቱ የነገ ተጋጣሚዎች ከዚህ ቀደም 25 ጊዜ ሲገናኙ ሁለቱም በእኩሌታ 9 ጨዋታዎች ላይ ድል አድርገዋል፤ 7 ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። መቻል 23፣ ሲዳማ 21 ጎሎች አስቆጥረዋል።