ግዙፉ የሀገር በቀል የስፖርት ትጥቅ አምራች የሆነው ጎፈሬ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ስር በሚዘጋጁ ሁሉም ውድድሮች ላይ ዳኞች የሚጠቀሙባቸውን ትጥቆች ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ለማቅረብ ስምምነት ፈፅሟል።
ዛሬ ከቀትር በኃላ በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተካሄደው በዚሁ መርሐግብር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ባሕሩ ጥላሁንን ጨምሮ የጎፈሬ መስራች እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የተከናወነ ነበር።
መርሐግብሩ ጅማሮውን ያደረገው የጎፈሬ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ፍፁም ክንድሼ ስለ ስምምነቱ ባደረጉት ገለፃ ሲሆን በገለፃቸውም ስምምነቱ ከሀገር አልፎ ምናልባት በአፍሪካ ደረጃ ፈርቀዳጅ ይሆናል ብለው የገለፁት ሲሆን ስምምነቱም ለሦስት ዓመታት የሚዘልቅ እንደሆነና ሁሉም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ስር ያሉ ዳኞች የሚታቀፉበት ስለመሆኑ አንስተዋል።
አቶ ፍፁም ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ በወንዶች ፕሪምየር ሊግ ለሚዳኙ ዳኞች አራት ዓይነት ትጥቆች በጎፈሬ ስፖንሰር አድራጊነት የሚቀርቡ ሲሆን በተጨማሪነትም በሌሎች የውድድር ዕርከኖች ለሚያጫውቱ ዳኞች ደግሞ ከወጭው ከፍ ያለው ድርሻ በጎፈሬ ስፖንሰር አድራጊነት ተሸፍኖ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አመላክተዋል።
በማስከተል ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሸዋንግዛው ተባበል ሲሆኑ በንግግራቸው ይህ ቀን ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ ዳኞች እጅግ ታሪካዊ ቀን መሆኑን አንስተው ዳኞቻችን ለዓመታት ይቸገሩበት የነበረውን አንዱን መሰረታዊ ችግር የቀረፈ ስምምነት ስለመሆኑ አንስተው ጎፈሬም በጋራ በማደግ እሳቤ ተመርኩዞ ከእነሱ ጋር መስራትን በመምረጡ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመቀጠል በዘንድሮው የውድድር ዘመን ጥቅም ላይ የሚውሉ አራት የቀለም አማራጭ ያላቸው ዳኞች በጨዋታ ወቅት የሚጠቀሙባቸው መለያዎች ፣ የማሟሟቂያ ቲሸርት ፣ የጉዞ ቲሸርት ፣ ቱታ በይፋ በተመረጡ በፕሪምየር ሊጉ በሚዳኙ ዳኞች ተዋውቀዋል።
በመርሐግብሩ መገባደጃ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ባሕሩ ጥላሁን እና የጎፈሬ መስራች እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን በይፋ ስምምነቱን በፊርማቸው ያፀኑ ሲሆን በማስከተልም በስፍራው ከተገኙ የመገናኛ ብዙኃን አባላት ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች በሁለቱ ተፈራራሚዎች አማካኝነት ምላሽ በመስጠት መርሐግብሩ ፍፃሜውን አግኝቷል።