አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ እና ድሬዳዋ ከተማ በአስደናቂ አጀማመራቸው ቀጥለዋል ፤ ሁለት ጨዋታ ሁለት ድል።
ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ የመክፈቻ መርሃግብር ድል ያደረገውን የመጀመሪያ 11 በማስቀል በጀመሩት ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በመብራት መቋረጥ ምክንያት ለ10 ያክል ደቂቃዎች ጨዋታው ለመቋረጥ ተገዷል።
በጨዋታው በደጋፊያቸው ፊት የሚጫወቱት ድሬዎች መሪ ለመሆን 6 ደቂቃ ብቻ ነበር የጠበቁት ፤ አብዱሰላም የሱፍ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ቻርልስ ሙሴጌ በግሩም አጨራረስ ድሬን መሪ አድርጓል።
ድሬዎች ከአምስት ደቂቃ በኋላ ሁለተኛ ግባቸውን አግኝተዋል ፤ ቢኒያም ገነቱ በረጅሙ የተጣለን ኳስ ለማቋረጥ ግቡ ለቆ መውጣቱን ተከትሎ በሰራው ስህተት ታግዞ ቻርልስ ሙሴጌ የቡድኑን መሪነት ከፍ አድርጓል።
ከግቧ መቆጠር በኃላ በተወሰነ መልኩ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች ድሬዳዋ ከተማዎችን ለመቋቋም ተቸግረው ተሰውሏል ፤ 35ኛው ደቂቃ ላይ ጀሚል ያዕቆብ ከቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት ወደ ውስጥ ያሳለፈለትን ኳስ መሀመድኑር ናስር ተንሸራቶ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ወደ ሦስት ከፍ አድርጓል።
ከዕረፍት መልስ ይበልጥ አውንታዊ ሆነው መጫወት የጀመሩት ድቻዎች አጋማሹን ካርሎስ ዳምጠው ከሳጥን ውጭ መቶ የግቡ አግዳሚ በመለሰበት ሙከራ ቢጀምሩም በ58ኛው ደቂቃ አራተኛ ግብ አስተናግደዋል ፤ አብዱሰላም የሱፍ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ መሀመድኑር ናስር በግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሯል።
የድሬዳዋ ከተማዎች ፍፁም የበላይነት በታየበት ወላይታ ድቻዎች ከባዶ መሸነፍ የዳኑበትን ግብ በ74ኛው ደቂቃ በአብዩ ካሳዬ ስህተት ታግዘው በያሬድ ዳርዛ አማካኝነት በማስቆጠር ጨዋታው በብርቱካናማዎቹ የ4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በመስመሮች በኩል የነበረውን እንቅስቃሴ መቆጣጠር አለመቻላቸው እና አስቀድመው ያስተናገዷቸው ግቦች ጨዋታውን ከእጃቸው እንዳወጣባቸው ገልፀዋል። አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው ጥሩ ጊዜ ማሳለፋቸውን አንስተው በማሸነፍ ውስጥ የሚያርሟቸው ክፍተቶች ስለመኖራቸው አንስተዋል አያይዘውም ግቦች ከተለያዩ አቅጣጫዎች መቆጠራቸው ጥሩ ስለመሆኑ አንስተዋል።