ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች |  መድን ከ ድሬዳዋ ከተማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | መድን ከ ድሬዳዋ ከተማ

ኢትዮጵያ መድን እና ድሬዳዋ ከተማ በ25 ቀናት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የሚያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ መቋጫ መርሐ-ግብር በሊጉ አናት እንዲሁም ግርጌ ባለው ፉክክር ምክንያት ተጠባቂ ነው።

በሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ጨዋታ በወላይታ ድቻ ሽንፈት ያስተናገዱት እና ሊጉን በሰላሣ አምስት ነጥቦች በመምራት ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች ከተከታዮቻቸው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስድስት ከፍ ለማድረግ በመጀመርያው ዙር የመጨረሻው ጨዋታ እንዲሁም በኢትዮጵያ ዋንጫ ላይ ያገኙትን ድሬዳዋ ከተማ ይገጥማሉ። መድን ከመጨረሻዎቹ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥቦች ሦስቱን ብቻ በማሳካት መጠነኛ መቀዛቀዝ ገጥሞታል፤ ድሬዳዋ ከተማን በሚገጥመት የነገው ጨዋታም የነጥብ ልዩነቱን ከፍ አድርጎ በመሪነቱ የሚደላደልበት ዕድል የሚፈጥርለት እንደመሆኑ ጨዋታው ተጠባቂ ያደርገዋል።

ባለፉት 25 ቀናት ድሬዳዋ ከተማን በገጠሙባቸው የሊግ እና የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች አምስት ግቦች በማስቆጠር በሁለቱም ጨዋታዎች ድል ያደረጉት መድኖች በነገው ጨዋታ ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ ባይገመትም ተጋጣሚያቸው ባለው የወራጅ ቀጠና ስጋት ጨዋታው ሌላ መልክ የሚይዝበት ዕድልም አለ።

በሀያ አንድ ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ባለፉት ዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት ከድል ጋር ተራርቀዋል።

በወራጅ ቀጠና ካለው ሀዋሳ ከተማ በሁለት ነጥቦች ብቻ የሚልቀው ቡድኑ የቅርብ ሳምንታት ውጤት አልባ አካሄዱ ያለፉትን ዓመታት የመጨረሻ ሳምንታት ውጥረት ውስጥ ዳግም እንዳይከተው ያሰጋዋል። ሲዳማ ቡናን ሦስት ለአንድ ካሸነፉ በኋላ ለዘጠኝ ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ማግኘት ያልቻሉት ብርቱካናማዎቹ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻሉት የግብ መጠን ሦስት ብቻ ነው፤ በመጀመርያዎቹ ሳምንታት ጠንካራ የነበረው የማጥቃት አጨዋወት በዚህ ልክ መዳከሙም በቡድኑ ውጤት አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። የፊት መስመራቸውን ለማጠናከር በዝውውር መስኮቱ አቡበከር ወንድሙ እና ዮሐንስ ደረጄን የግላቸው ያደረጉት ድሬዳዋ ከተማዎች የሊጉ ዝቅተኛው የግብ መጠን ያስተናገደ እና ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው የሊጉ መሪ መድን በሚገጥሙበት ጨዋታ በሁሉም ረገድ የተሻሻለ ብቃት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 9 ጊዜ ሲገናኙ መድን 4 ጨዋታዎች ላይ ድል ሲቀናው ድሬዳዋ ከተማ 3 ጨዋታዎች አሸንፏል፤ የተቀሩት 2 ግንኙነቶች ደግሞ በነጥብ መጋራት የተደመደሙ ነበሩ ። በጨዋታዎቹ መድን 15 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 7 ግቦችን አስቆጥረዋል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል ተመስገን ደረስ፣ ስያም ሱልጣን፣ ያሬድ ታደሰ እና መሐመድኑር ናስር በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም። በኢትዮጵያ መድን በኩል ያለው የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።