​የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት – የእሁድ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

ከተጀመረ ሦስተኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሦስተኛው ሳምንት ከሚያስተናግዳቸው ጨዋታዎች አምስቱ ነገ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ቀጥለው የሚካሄዱ ይሆናል። አምስቱን ጨዋታዎች እንደሚከተለው ዳሰናቸዋል።

ጅማ አባ ጅፋር ከ ፋሲል ከተማ

በአዲስ አባባ ከተማ ዋንጫ ላይ በመሳተፍ ጥሩ የቅድመ ውድድር ጊዜ ያሳለፈው ጅማ አባጅፋር ሊጉን ሜዳው ላይ ሀዋሳ ከተማን ድል በማድረግ ቢጀምርም በሁለተኛ ሳምንት ጨዋታው በድሬደዋ ከተማ ተሸንፏል። አምና ሊጉን ተቀላቅሎ የውድድሩ ክስተት ሆኖ ያለፈው ፋሲል ከተማ በበኩሉ በመጀመሪያ ሳምንት ከሜዳው ውጪ ከወልዋሎ ዓ.ዩ ጋር ነጥብ ተጋርቶ በሁለተኛው ሳምንት ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር በሜዳው ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ በመተላለፉ በድጋሜ ከሜዳው ውጪ አባጅፋርን የሚገጥም ይሆናል።
ጠንካራ የቡድን መዋቅር ያለው ጅማ አባጅፋር በቀላሉ ግብ የማይስተናግድ የኃላ መስመር እና ለመልሶ ማጥቃት የሚመች የአማካይ ክፍል ያለው ቡድን ነው። ጨዋታውን ሜዳው ላይ እንደማድረጉ እና ከሽንፈት እንደመመለሱም ቡድኑ ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አቀራረብ እንደሚኖረው ይገመታል። በመጀመሪያ ጨዋታው ከሜዳው ውጪ በሊጉ ባልተለመደ ሁኔታ ሁለት ግቦችን አስቆጠረው የተመለሱት ፋሲሎችም በነገው ጨዋታ ላይ በጥሩ የማጥቃት ፍላጎት ጨዋታውን እንደሚጀምሩ ይጠበቃል። ይህ ነጥብም ጨዋታውን በሳምንቱ ግቦችን ከጥሩ ፉክክር ጋር ሊያሳዩን ከሚችሉ ጨዋታዎች አንዱ ያደርገዋል።

ያሬድ ባዬ እና ዳዊት እስጢፋኖች አባጅፋርን በሚገጥመው የአፄዎቹ ስብስብ ውስጥ ይልተካተቱ ሲሆን የአባጅፋሮቹ ጌቱ ረፌራ እና ዝናቡ በጉዳት በዚህ ጨዋታ ላይ የማይገኙ ሲሆን የኦኪኪ አፎላቢ እና እንዳለ ደባልቄ መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል።

ይህን ጨዋታ ፌደራል ዳኛ ሚካኤል አረአያ በመሀል ዳኝነት እንደሚመራው ይጠበቃል


አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

አምና በርካታ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት በመደምደም ቅድሚያውን የወሰደው አርባምንጭ ከተማ ዘንድሮም በሁለት ተከታታይ አቻ ውጤቶች ለሶስተኛው ሳምንት ደርሷል። አንድ ጨዋታ ብቻ ያደረገው ኢትዮ ኤሌክትሪክም እንዲሁ በመጀመሪያው ሳምንት ከመከላከያ ጋር 1-1 መለያየቱ የሚታወስ ነው። ሆኖም በ2009 የውድድር አመት 20ኛው ሳምንት ላይ ሁለቱ ቡድኖች አርባምንጭ ላይ ሲገናኙ ባለሜዳው በአማኑኤል ጎበና እና ፀጋዬ አበራ ጎሎች 2-0 አሸንፎ ነበር።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም በአርባምንጭ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት የሚያደርጉት ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት ይጠናቀቃሉ ተብለው ቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው ጨዋታዎች መሀከል አንዱ ነው። ሁለቱም ቡድኖች በርከት ያሉ አማካዮችን በመጠቀም የሚታወቁ መሆናቸው የጨዋታው አሸናፊነት ምናልባትም የመሀል ሜዳውን የበላይነት ወደ ሚቀዳጀው ቡድን እንደሚያጋድል ይገመታል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል የአልሀሰን ካሉሻ እና ዲዲዬ ለብሪ ጥምረት ተጠባቂ ሲሆን የአርባምንጩ የፊት አጥቂ ላካ ሳኒም ከነወንድሜነህ ዘሪሁን ጋር የሚኖረው ቅንጅት በጨዋታው ተጠባቂ ነው።

በሁለቱ ቡድኖች የአምናው ግንኙነት ላይ ግብ ያስቆጠረው አማኑኤል ጎበና ከአርባምንጭ በኩል በጉዳት የማይሰለፍ ይሆናል። በኤሌክትሪክ በኩል እስካሁን ለአዲሱ ክለባቸው ያልተሰለፉት ቢኒያም አሰፋ እና ኃይሌ እሸቱ ጨዋታው የሚያፋቸው ሲሆን በሊጉ መክፈቻ ጉዳት የገጠመው ሱሊማን አቡም ለጨዋታው መድረሱ አጠራጣሪ ሆኗል።
ጨዋታው በፌደራል ዳኛ ቢንያም ወርቅአገኘው የመሀል ዳኝነት ይሚመራ ይሆናል።


ወላይታ ድቻ ከ አዳማ ከተማ

አምና በተመሳሳይ ሦስተኛ ሳምንት ላይ ተገናኝተው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች ዘንድሮ ወላይታ ድቻን ለቆ አዳማ ከተማን በተቀላቀለው የፊት አጥቂው አላዛር ፋሲካ ብቸኛ ጎል ጨዋታቸውን ሲደመድሙ ለባለሜዳዎቹ የአመቱ ሁለተኛ ተከታታይ ድል ሆኖ ተመዝግቦ ነበር። እንደአምናው ሁሉ ዘንድሮም መልካም አጀማመር ማድረግ የቻለው ወላይታ ድቻ ባረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ሰብስቦ ሊጉን መምራት ችሏል። በአንፃሩ የአሰልጣኝ ተገኔ ነጋሹ አዳማ ወልድያ ላይ ሊጉን በሽንፈት ሲጀምር ሳምንት ከደደቢት ጋር አቻ በመለያየት የመጀመሪያ ነጥቡን አሳክቷል።

ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየተሻሻለ የመጣው የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድን በሜዳው በሚያደርገው የመጀመሪያ ጨዋታ አዳማን ሲያስተናግድ በመከላከያው ጨዋታ ላይ እንደታየው ሁሉ ወደፊት ለመሄድ ድፍረት ባላቸው የመስመር ተመላላሾቹ የሚታገዝ የማጥቃት አጨዋወትን እንደሚተገብር ይጠበቃል። ጥሩ አቋም እያሳየ የሚገኘው ጃኮ አራፋትም ተደጋጋሚ ስህተት ሲሰራ ለታየው የአዳማ ከተማ የተከላካይ መስመር ፈተና እንደሚሆን ይታመናል። አዳማ ከተማ ምንም እንኳን የአማካይ ክፍሉን ከአምናው በተሻለ መልኩ ቢያዋቅርም አጥቂ መስመር ላይ ያለበት የተጨዋች እጥረት ግቦችን እንዳያገኝ ምክንያት የሆነው ይመስላል። በርግጥ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ለመከላከል ቅድሚያ ቢሰጥም የዳዋ ሁቴሳን አገልግሎት ከቤሔራዊ ቡድን መልስ ማግኘቱ በእጅጉ እንደሚጠቅመው ይጠበቃል።
የወላይታ ድቻዎቹ ዳግም በቀለ እና በዛብህ መለዮ በጉዳት ከዚህ ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ሳምንት በሁለት ቢጫ ከሜዳ የወጣው ተስፋዬ ነጋሽን ጨምሮ ቡልቻ ሹራ ፣ ታፈሰ ተስፋዬ እና ሲሳይ ቶሊ ደግሞ በአዳማ ከተማ በኩል አገልግሎት የማይሰጡ ተጨዋቾች ይሆናሉ።
ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመራው ፌደራል ዳኛ ሳህሉ ይርጋ ይሆናል።

ደደቢት ከ ሀዋሳ ከተማ

ከሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች መሀከል መልካም እንቅስቃሴ ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀውን ይህን ጨዋታ የሚያስተናግደው ደደቢት በሁለቱ የቀደሙ ጨዋታዎቹ ግብ ማስቆጠር ባይችልም ሁለት ነጥቦችን ግን ማሳካት ችሏል። በተቃራኒው ሳምንት በወልድያ መረብ ላይ አራት ግቦችን ያስቆጠረው ሀዋሳ ከተማ በመጀመሪያ ሳምንት በጅማ አባጅፋር ከደረሰበት ሽንፈት ማገገም ችሏል።

ሳምንት ከአዳማ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ አምስት አማካዮችን ከአቤል ያለው ጀርባ በመጠቀም የተሻለ የመሀል ክፍል ጥንካሬን ያሳየው ደደቢት ከጌታነህ መመለስ በኃላ በምን አይነት ቅርፅ ወደ ጨዋታው እንደሚቀርብ ይጠበቃል። ከሀዋሳ ከተማ ጠንካራ የአማካይ ክፍል ጋር የሚገናኝበት ይህ ጨዋታም የቡድኑን የግብ ዕድሎች የመፍጠር ብቃት ዳግም የሚፈትሽበት ይሆናል። እስካሁን ግብ ማስቆጠር ያልቻለው የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ቡድን አምና በዚሁ ጨዋታ ላይ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ የነበረውን ጌታነህ ከበደን ከቤሔራዊ ቡድን አገልግሎት በኃላ ማግኘቱ ይህንን ድክመቱን ለመቅረፍ እንደሚረዳው ይታመናል። ከሜዳ ውጪ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ለማጥቃት ፍላጎት ከሚያሳዩ ጥቂት ቡድኖች መሀከል አንዱ የሆነው ሀዋሳ ከተማም አቀራረቡ ከወትሮው የተለየ እንደማይሆን ይገመታል።

ይህም ጨዋታው ለተመልካች አዝናኝ የሚሆን እና ግቦችም የሚቆጠሩበት ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም ነው። ሳምንት ሶስት ግቦችን በማስቆጠር የሊጉን ከፍተኛ ግብ አግቢነት መምራት የጀመረው ዳዊት ፍቃዱም አምና በብዙ አወዛጋቢ ጉዳዮች ታጅቦ ያልተሳካ የውድድር አመት ያሳለፈበትን ደደቢትን መግጠሙ የጨዋታው ትኩረት ሳቢ ጉዳይ ሆኗል።

ከሀዋሳ ከተማ በኩል ዳንኤል ደርቤ እንዲሁም ከደደቢት ኩዌኪ አንዶህ በጉዳት ምክንያት ለጨዋታው እንደማይደርሱ ታውቋል።

ፌደራል ዳኛ በፀጋ ሽብሩ የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ እንደሚመራ ይጠበቃል።


ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መቐለ ከተማ

ሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አዳጊው መቐለ ከተማን የሚያስተናግድበት ይህ ጨዋታ ሦስተኛውን ሳምንት የሚያሳርግ ይሆናል። መቐለ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ ጋር ነጥብ በመጋራት ሊጉን ሲጀምር ቅዱስ ጊዮርስጊስ ከድሬደዋ ከተማ እና ፋሲል ከተማ ጋር የነበሩት ጨዋታዎች ለሌላ ጊዜ መተላለፋቸው የሚታወስ ነው።

አሰልጣኝ ዮሀንስ ሣህሌ በመጨረሻ ሰዐት ላይ የተረከቡት የመቐለ ምንም እንኳን ከመከላከያ እና አዲስ አበባ ከተማ ጋር ያደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ቢጠቅመውም ቡድኑን በውድድር ላይ በመገንባት ላይ እንዳለ ግን ግልፅ ነው። ኳስ መስርቶ በመጫወት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚሞክረው ቡድኑ እስካሁን በሊጉ ግብ ማስቆጠር አልቻለም። በርግጥ  ከወልዋሎ ዓ.ዩ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ የአማካይ ክፍሉ በርካታ ዕድሎችን ሲፈጥር ቢታይም ኳስ እና መረብ ሳያገናኝ ቀርቷል። በተመሳሳይ በአዲስ አሰልጣኝ የውድድር አመቱን የሚጀምረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአሰልጣኝ ቫዝ ፒኒቶ ስር የአጨዋወት ለውጥ በማድረግ ቀድሞ ከሚታወቅበት ቀጥተኛ እና የመስመር ኳሶች ውጪ እንደተጋጣሚው ሁሉ ኳስን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት አድርጓል። በዚህም መሰረት መሀል ሜዳ ላይ የሚኖረው የቡድኖቹ ፉክክር የሚጠበቅ ሲሆን ያሬድ ከበደ ከሙላለም መስፍን እንዲሁም መስመር ላይ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከአብዱልከሪም መሀመድ የሚገናኙባቸው ቦታዎች በጨዋታው ተጠባቂ ይሆናሉ። የቅዱስ ጊዮርጊስ የአጥቂ አማካዮችም ከሚካኤል ደስታ እና ባልተገመተ መልኩ የተከላካይ አማካይነት ሚና ከተሰጠው ዐመለ ሚልኪያስ ጋር የሚያደርጉት ትንቅንቅም ትኩረትን ይስባል።
በእንግዶቹ መቐለዎች በኩል የተሰማ የጉዳት ዜና ባይኖርም የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ሳላዲን ሰይድ ፣ በሀይሉ ግርማ ፣ አስቻለው ታመነ እና ማሊያዊው አጥቂ ሲዲ መሐመድ በጉዳት ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ይሆናል። ከዚህ ውጪ  የአምበሉ ደጉ ደበበ መሰለፍ አጠራጣሪ ሲሆን ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኘው ታደለ መንገሻም ከጨዋታው ውጪ ነው።

ይህን ጨዋታ ፌደራል ዳኛ አማኑኤል ወ/ፃዲቅ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *