‹‹ትልቅ ግብ ጠባቂ መሆን የምንችለው እድል ሲሰጠን ነው ›› ፅዮን መርዕድ

ፅዮን መርዕድ ይባላል። ተስፋኛ ግብ ጠባቂ ነው። ያለፉትን ሁለት አመታት ለአርባምንጭ ከተማ አራተኛ ግብ ጠባቂ በመሆን እያገለገለ ይገኝ ነበር ። አርባምንጭ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት የተረከቡት እዮብ ማለ ቡድኑን ማሰልጠን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በመጀመርያ ተሰላፊነት እየተሰለፈ የሚገኝ ሲሆን በቡድኑ ለታየው መሻሻል አስተዋፆ እያደረጉ ከሚገኙ ተጨዋቾች መካከልም አንዱ ሆኗል።

አሰልጣኝ እዮብ ማለ አርባምንጭ ከተማ ውስጥ አመጡት ከሚባለው ለውጥ አንዱ የተጨዋቾችን አጠቃቀም ነው። በዚህ የተጨዋቾች ለውጥ ሂደት ደግሞ አሰልጣኙን በማሳመን ያለፉትን አራት ጨዋታዎች የቋሚ ተሰላፊነት ዕድል በማግኘት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ፅዮን መርዕድ ነው ። የተጫዋቹን አቅም ያጎላው ደግሞ ያለፉትን 10 አመታት በግብ ጠባቂነት የረዥም አመት አገልግሎት በመስጠት ልምድ ያላቸውን አንተነህ መሳን ፣ ጃክሰን ፊጣ እና ሲሳይ ባንጫን በተቀያሪ ወንበር ላይ አሰቀምጦ  የቋሚ ተሰላፊነት ዕድል እያገኘ መሆኑ ነው ። በዚህ ሳምንት የተስፈኞች አምድ ዝግጅታችን የዚህ ተስፈኛ ታዳጊ ግብ ጠባቂ እድገት እና የወደፊት ጉዞ አስመልክቶ ያደረግነውን ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል ።


ትውልድና እድገትህ የት ነው? ግብጠባቂ የመሆን አጋጣሚውን እንዴት አገኘኸው ?

ተወልጄ ያደኩት እዚሁ አርባምንጭ ከተማ ልዩ ስሙ ምዕራብ አባያ የሚባል ቦታ ነው። ሰፈራችን አቅራቢያ በሚገኝ ትምህርት ቤት ውስጥ በፕሮጀክት ታቅፌ ነው እግርኳስን መጫወት የጀመርኩት። ከ17 አመት በታች የጋሞ ጎፋ ፕሮጀክትን ወክዬ ወደ ሀዋሳ ከመሄዴ በፊት በመጀመርያ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች የነበርኩ ሲሆን በኋላ ላይ ነው ወደ ግብ ጠባቂነት ተቀይሬ መጫወት የጀመርኩት ።


ከቤተሰብህ እግርኳስን ተጫውቶ ያለፈ አለ? እስኪ ስለ ቤተሰብህ አጫውተኝ።

ከቤተሰቤ ከዚህ ቀደም እግርኳስን ተጫውቶ ያለፈ ባይኖርም አባቴ መርዕድ በጣም ሲበዛ እግርኳስን የሚወድ ሰው ነው። በክለብ ደረጃ ተጫውቶ አይለፍ እንጂ ለሚሰራበት መስሪያ ቤት እግርኳስን ይጫወት ነበር። እሱ ነው ተጨዋች እንድሆን በጣም እየገፋፋ ያስጀመረኝ።  ከልጅነቴ ጀምሮ እስካሁን የእርሱ እገዛ አልተለየኝም። ለቤተሰቤ የመጀመርያ ልጅ ነኝ። ከእኔ በታች ያለው ወንድሜ ይሁን መርዕድ ይባላል በአሁን ሰአት ለወላይታ ድቻ ከ17 አመት በታች ቡድን ግብጠባቂ በመሆን እየተጫወተ ይገኛል። ሌላው የመጨረሻ ወንድሜም እንዲሁ ኳስን እየተጫወተ የሚገኝ ታዳጊ ነው ።


አርባምንጭ ከተማን ከመቀላቀልህ አስቀድሞ የነበረው የእግርኳስ ጊዜህ ምን ይመስላል?

እንዳልኩህ እዚህ አርባምንጭ ላይ በነበረ የታዳጊ ፕሮጀክት እየሰራው 2005 ላይ ሀዋሳ ከተማ ላይ በተካሄደው የደቡብ ከ17 አመት በታች ውድድር የጋሞ ጎፋን ፕሮጀክት  ወክዬ በመሄድ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን መመለስ ችያለው። ከዚህ በኋላ እዚህ ዕድገቴን የሚያስቀጥል ክለብ የሌለ መሆኑ ወደ ሀላባ መስመር በሚገኝ ሳንኩራ ለሚባል ቡድን በብሔራዊ ሊግ ደረጃ መጫወት ችያለው። እዛም አንድ አመት ከቆየው በኋላ ተመልሼ ወደዚህ መጣው። እዚህ የመጣውትም በሙከራ ነበር። ሙከራውን አልፌ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር አብሬ መስራት ከጀመርኩ አሁን ሦስተኛ አመቴ ነው።


አርባምንጭ ከተማ ከታች ጀምሮ ታዳጊዎችን ይዞ የሚያሳድግበት ቡድን አለመኖሩ ጉዳት አለው ትላለህ?  አንተ እድገቴን የሚያስቀጥል ክለብ ሳጣ ወደ ሳንኩራ ብሔራዊ ሊግ ቡድን ሄጃለው ስላልከኝ።

ትልቁ ክፍተት ይሄ ነው። ታዳጊዎች በየዕድሜያቸው የሚያዙበት የተስፋ ቡድን የለም። ከዚህ ቀደም ነበር ነገር ግን አይቆይም ይፈርሳል ። በዚህም ምክንያት ብዙዎች አቅም እያላቸው ጠፍተዋል። ወደ ወላይታ ሶዶ እና ሌሎች ክለቦች እየሄዱ ነው። በሌሎች ክለቦች በየዕድሜ እርከኑ ከስር ቡድኖች አሉ። አርባምንጭ ላይ ግን ይሄ የለም። ይህ መሆኑ ደግሞ ወደ ፊት የሚጎዳው ራሱ ክለቡን ነው። ከፍተኛ ብር እያወጡ የክለቡን አቅም ከሚያዳክሙ እዚህ ያሉ ታዳጊዎች ላይ ስራ ሊሰራበት ይገባል እላለው። እዚህ ታዳጊ ላይ መስራት በጣም ይቀራል። አሁን በአዲስ መልክ የተዋቀሩት ኮሚቴዎች ይህንን ነገር በሚገባ ያስተካክሉታል ብዬ ተስፋ አደርጋለው ።


የአርባምንጭ ከተማ የ3 አመታት ቆይታ ምን ይመስላል?

ለእኔ መልካም ቆይታ ነው። ሁሌም ራሴን ለማብቃት ጠንክሬ እሰራ ነበር። የመጣሁት ሙከራ በማድረግ ነበር። ሙከራውን አልፌ አራተኛ ግብ ጠባቂ ሆንኩ። ታዲያ አንድ ቀን በቡድኑ ውስጥ በቋሚነት የመሰለፍ እድል እንደማገኝ እምነቴ ነበር። አምና እንዲያውም ወደ መጨረሻ የውድድር ጊዜ አካባቢ ላይ በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ እድል አግኝቻለው። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በአዲሱ አሰልጣኝ የቋሚ ተሰላፊነት እድል አግኝቼ ጥሩ ነገር ለመስራት እየሞከርኩ እገኛለው።


አርባምንጭ ከተማ በጊዛዊነትም ቢሆን ከወራጅ ቀጠና እንዲወጣ እና ቡድኑ መሻሻል እንዲያሳይ ካደረጉ ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነህ። ይህን እንቅስቃሴህን እንዴት ታየዋለህ ?

አሁን ላይ ያለው ነገር ጥሩ ነው። ቡድናችንም እያስመዘገበ ያለው ውጤት አሪፍ ነው። እኔም በግሌ ቡድኔ ውጤታማ እንዲሆን እሰራለው። እነ ሲሳይ ባንጫ ትልቅ ልምድ ይሰጡኛል። ከእነርሱ ብዙ ነገር እማራለው። ገና ብዙ የሚቀረኝ ታዳጊ ተጨዋች ስለሆንኩ በቀጣይም አቋሜን ጠብቄ ቡድኑን ከዚህ በላይ ለማገልገል ጥሩ ነገር እሰራለው ብዬ አስባለው ።


ግብ ጠባቂነት ኢትዮጵያው ውስጥ የሚሰጠውን ትኩረት እንዴት ታየዋለህ ?

ኢትዮጵያ ውስጥ የግብ ጠባቂ ችግር አለ ተብሎ ይነገራል። ነገር ግን በጣም ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። አቅም እያላቸው ብዙዎቹ የመሰለፍ እድል ማግኘት አልቻሉም። ትልቅ ግብ ጠባቂ መሆን የምንችለው የመጫወት እድል ሲሰጠን እኮ ነው። ይህ በሌለበት ሁኔታ በረኛ የለም ይባላል። እድል ከተሰጠን ብዙ ነገሮችን መስራት እንችላለን ። እኛ ሀገር ታዳጊ ናቸው ፤ ብዙ ልምድ የላቸው እየተባለ በረኞችን ያስቀምጣሉ። ግብ ጠባቂነት እንደ ሜዳ ላይ ተጨዋች አይደለም። የተወሰነ ደቂቃም ቢሆን መጫወት ስትችል ነው ልምድ የምታገኘው። ስለዚህ ክለቦች ለግብ ጠባቂዎች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል።


በቀጣይ በቋሚ ተሰላፊነት ለመቀጠል እና የተሻለ ደረጃ ለመድረስ ምን ታስባለህ ?

አዎ ብዙ ነገር አስባለው። በግሌ የራሴ የልምምድ ፕሮግራም አለኝ። ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ሀገር ስልጠናዎችን ፊልም አውርጄ ቁጭ ብዬ ራሴን ለማሳደግ እመለከታለው። ከዚህ ውጭ አጠገቤ ካሉት ከእነ ሲሳይ ባንጫ የህይወት ልምድ እወስዳለው ፣ እማራለው ። ራሴን በስነ ምግባር ጠብቄ  በቀጣይ ትልቅ ደረጃ መድረስ እፈልጋለው። ከክለብ አልፎ እሰከ ኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ድረስ ።


በግብጠባቂነት ምሳሌ የምታደርገው ተጨዋች አለ ?

በስም ነበር የማቀው አሁን አብሬ እየሰራው የምገኘው ሲሳይ ባንጫ እንዲሁም ጀማል ጣሰው በጣም አደንቃቸዋለው። ከውጭ ሀገር በረኞች እዚህ ሲመጣ ጠብቄ የምመለከተው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሮበርት ኦዶንካራን ነው። በጣም ጥሩ ነገር አላቸው ።


አሁን ላለህበት ደረጃ መድረስ ትልቁን አስተዋፆኦ ያደረገልህ አካል አለ ?

ከአባቴ በላይ ይሄንን ዋጋ የሚወስድ የለም። ከልጅነቴ ጀምሮ ይዞ ወደ ሜዳ እንዲሁም ዲኤስ ቲቪ ቤት እየወሰደኝ ኳስ እንድወድ ያደረገኝ ሁሌም ጠንክሬ እንድሰራ የሚመክረኝ እሱ ነው። ጨዋታ ባለበት ቀን ሁሉ ሜዳ እየመጣ ያበረታታኛል። ከጨዋታም በኋላ ማድረግ ያለብኝን ነገር የሚነገረኝ አባቴ ነው። ለእኔ ፈጣሪና አባቴ ባለውለታዎቼ ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *