ሳላዲን ሰዒድ በዚህ አመት ወደ ሜዳ አይመለስም

የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ሳላዲን ሲዒድ ክለቡ አምና ሐምሌ ወር በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ጨዋታ ከደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ ባጋጠመው የጉልበት ጉዳት ይህን አመት ለፈረሰኞቹ መስጠት የሚገባውን አገልግሎት ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡

ሳላዲን ከሜዳ ከራቀ ከስድስት ወር በኋላ ዳግም በቻምፒየንስ ሊጉ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ ከዩጋንዳው ኬሲሲኤ ጋር በአዲስ አበባ ስታድየም ተቀይሮ ገብቶ ለመጀመርያ ጊዜ መጫወት ችሎ ነበር ። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ነበር በጨዋታው ላይ ዳግመኛ የተጎዳው። ሳላዲን ሰኢድ በሀገር ውስጥ ህክምና ብዙም ደስተኛ ባለመሆኑ ከኢትዮዽያ ውጭ የተሻለ ህክምና ለማግኝት ወደ ጀርመን ነገ የሚያቀና ይሆናል።

ሳላዲን ከኬሲሲኤ በተደረገው ጨዋታ ተቀይሮ ቢገባም ጉዳቱ አገርሽቶበታል

አምና በቻምፒየንስ ሊጉ 7 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለው ሳላዲን ስላገረሸበት ጉዳት እና ስላሳለፈው ከባድ ጊዜ ለሶከር ኢትዮጵያ በሚከተለው መልኩ ተናግሯል፡፡

‹‹ ይህ አመት ለእኔ ከባድ ጊዜ ነበር ። እግርኳስ ተጨዋች ስትሆን እንዲህ ያሉ የማትጠብቃቸው ከባድ ጊዜዎች ያጋጥሙሀል፡፡ ሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ ህክምናዬ ተከታትያለው፡፡ ሆኖም የሚሰጡኝ ውጤት (ምላሽ) ተገቢ አልነበረም፡፡ MRI በምርመራ አደርግ ነበር ፤ ውጤቱ ግን በትክክል ጉዳቴን የሚገልፅ አለመሆኑ በፍጥነት ወደ ሜዳ እንድመለስ አድርጎኛል ። አሁን ጥሩ ህክምና እንደማገኝ በመተማመን ነገ ወደ ጀርመን እሄዳለው ። በጀርመንም በሚኖረኝ የሁለት ሳምንት ቆይታ ከፍተኛ የሚባል የጉልበት ቀዶ ጥገና አደርጋለው ። ሰርጀሪው ከበድ ያለ በመሆኑ እና ከዚህ በኋላም የማገገሚያ ጊዜ ስድስት ወር ስለሚያስፈልገው በዚህ አመት ወደ ሜዳ አልመለስም ። ከፈጣሪ ጋር ከሙሉ ጤንነት ወደ ሜዳ እመለሳለው ብዬ ተስፋ አደርጋለው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *