ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ አርባምንጭ ከተማ

ከቅዳሜ ጀምሮ ሲካሄድ የሰነበተው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ዛሬ የመጨረሻ ጨዋታውን በማስተናገድ ይቋጫል። 9፡00 ላይ በዓዲግራት የሚጀምረውን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ሁለቱ ክለቦች ባሳለፍነው አርብ በኢትዮጵያ ዋንጫ እዛው ዓዲግራት ላይ ተገናኝተው በመለያ ምቶች አርባምንጭ ካሸነፈ በኃላ ነው ዛሬ በድጋሜ በሊጉ የሚጫወቱት። ሌሎች የወራጅ ቀጠና ተፎካካሪዎቻቸው የሆኑት ድሬደዋ ከተማ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዲያ በዚህ ሳምንት ሽንፈት ማስተናገዳቸው ደግሞ የጨዋታውን ግምት እጅግ ከፍ አድርጎታል። ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች ባለፉት ሳምንታት እያስመዘገቡ የመጡት ውጤት ደካማ የሚባል ነው። ድል ካስመዘገበ ከሁለት ወራት በላይ ጊዜን ያስቆጠረው ወልዋሎ ዓ.ዩ በሪችሞንድ አዶንጎ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ ከመጋራቱ በቀር ከተቋረጠው የመቐለ ጨዋታ ውጪ በሁለተኛው ዙር ሽንፈት ሲያስተናግድ ነው የከረመው። ከተጋጣሚው በተሻለ ሜዳው ላይ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በማሸነፍ ነጥቦችን እየሰበሰበ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማም ከሜዳው ውጪ ውጤት ይዞ መመለስ አለመቻሉ ደረጃውን እንዳያሻሻል ዕንቅፋት ሆኖበታል። ከነዚህ ነጥቦች አንፃር ቡድኖቹ ዛሬ እርስ በእርስ ከሚገናኙበት ጨዋታ የሚያገኙት ነጥብ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ለሚኖራቸው መሻሻል ትልቅ እገዛ ይኖረዋል።

ወልዋሎም ሆነ አርባምንጭ ወሳኙን ጨዋታ የሚያደርጉት ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነ ሙሉ ስብስባቸውን በመያዝ ነው። አርባምንጭ ከተማ ደግሞ ተመስገን ካስትሮን ከቅጣት መልስ ማግኘቱ ተጨማሪ ጥሩ ዜና ሆኖለታል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


የጨዋታው አጠቃላይ መልክ ወልዋሎ ዓ.ዩ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በመያዝ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚሞክርበት እንዲሁም አርባምንጭ ከተማ ከድንገተኛ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ግቦችን ለማግኘት የሚሞክርበት እንደሚሆን ይገመታል። በዚህ ሂደት ውስጥ ለወልዋሎ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና የሚወጣው የዋለልኝ ገብሬ እና አፈወርቅ ሀይሉ ጥምረት ከአርባምንጮቹ አማካዮች አማኑኤል ጎበና እና ምንተስኖት አበራ ጋር ይሚገናኝባቸው ቅፅበቶች ወሳኝ ይሆናሉ። ተጋጣሚዎች ፈጣን የማጥቃት ሽግግርን በሚያደርጉበት ሰዐት ክፍተት የሚታይበት የአርባምንጭ ከተማ የግራ እና ቀኝ የተከላካይ ክፍል ዛሬም በመሀል እና በመስመር ተከላካዮቹ መሀል የሚገኘው ቦታ ለወልዋሎ የመስመር አጥቂዎች የተመቸ እንዳይሆን ማድረግ ይጠበቅበታል። የባለሜዳዎቹ አዲስ ጠንካራ ጎን የሆነው የፊት አጥቂው ሪችሞንድ አዶንጎ ንፁህ የማይባሉ አጋጣሚዎችን ሳይቀር ወደ ሙከራነት መቀየር መቻሉ እና ከኳስ ውጪ ተከላካዮችን ቅብብል ለማቆረጥ የሚያደርገው ጥረት በተለይ ከተመስገን ካስትሮ ጋር የሚያደርጉትን ፍልሚያ ተጠባቂ ያደርገዋል።

ወጣት እና ፈጣን የፊት አጥቂዎችን የያዘው የአርባምንጭ የአጥቂ ክፍልም ለወልዋሎ ተከላካዮች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መፍጠር የሚከብደው አይመስልም። በተለይ ወልዋሎዎች ኳስ መስርተው ከሜዳቸው በሚወጡበት ጊዜ መሀል ላይ አርባምንጮች እንቅስቃሴያቸውን ማቋረጥ ከቻሉ ከተከላካዮች ጀርባ ወደ ፊት ሰብሮ ለመግባት የሚያስችል ክፍት ቦታ ማግኘታቸው የማይቀር ነው። መሰል አጋጣሚዎችን በመከላከሉ ረገድ ወልዋሎች ካለባቸው ድክመት አንፃር ከነእንዳለ ከበደ የሚነሱ ኳሶች ለዘካሪያስ ፍቅሬ እና ብርሀኑ አዳሙን ለመሳሰሉት አጥቂዎች ቀጥተኛ ሩጫ የተመቹ ሆነው መልካም አጨራረስ ከታከለባቸው ለአሰልጣኝ እዮብ ማለ ቡድን ጥሩ አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በሊጉ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ አርባምንጭ ላይ የተጋናኙበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ላኪ ሳኒ እና ወግደረስ ታዬ በመጨረሻ ደቂቃዎች ባስቆጠሯቸው ግቦች 1-1 የተጠናቀቀ ነበር።

– ወልዋሎ ዓ.ዩ ለመጨረሻ ጊዜ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች በሙሉ ግብ አስቆጥሮ መውጣት ቢችልም ማሳካት የቻለው ግን 1 ነጥብ ብቻ ነው።

– ወልዋሎ ዓ.ዩ 12ኛው ሳምንት ላይ ሀዋሳ ከተማን 1-0 ካሸነፈበት ጨዋታ ውጪ ግብ ሳይቆጠርበት ከሜዳ የወጣው በታህሳስ ወር መጨረሻ ከወልዲያ 0-0 በተለያየበት ወቅት ነበር።

– አርባምንጭ ከተማ በሁለተኛው ዙር ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሙሉ ሽንፈት ሲያስተናግድ ሰባት ጎሎች ተቆጥረውበት አንድም ጊዜ በተጋጣሚው ላይ ጎል ማስቆጠር አልቻለም።

ዳኛ

– ከአምናው አንፃር በርከት ባሉ ጨዋታዎች ላይ ሀላፊነት እየተሰጠው የሚገኘው ፌደራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት እንደሚመራ ተመድቧል።