የ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ተጀምሯል

በሁለት ምድብ ተከፍሎ የሚካሄደው የኢትዮዽያ ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር ውድድር ዛሬ ሲጀምር ኢትዮዽያ ቡና ፣ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ፣ ማራቶን እና ሲዳማ ቡና አሸናፊ ሆነዋል።

በምድብ ለ መድን ሜዳ 05:00 ላይ ኢትዮዽያ መድን እና ኢትዮዽያ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ በኢትዮዽያ ቡና 3-0 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል። ተመጣጣኝ ፉክክርን ከማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጋር ባስተናገደው የሁለት ቡድኖች ጨዋታ ቡናዎች ብልጫ በወሰዱባቸው ደቂቃዎች ውስጥ በአምበላቸው ፍራኦል ደምሰው ግሩም ጎል ቀዳሚ መሆን ሲችሉ ባለሜዳዎቹ መድኖች ከጎሉ መቆጠር በኋላ በጥሩ እንቅስቃሴ ወደ ጎል መድረስ ቢችልም ጎል እና መረብን የሚያገናኝ ሁነኛ አጥቂ አለመኖሩ ተከትሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የነበራቸው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። በዚህ ጥረታቸው መሀል ተከላካዮቹ የፈጠሩትን ስህተት ተጠቅሞ አጥቂው ተገኝ ዘውዱ ለኢትዮዽያ ቡና ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል። የጎሉ በራሳቸው ስህተት መቆጠሩም በመድን በኩል የነበራቸውን የመጫወት ተነሳሽነት አወርዶ የመጀመርያው አጋማሽ በኢትዮዽያ ቡና 2-0 መሪነት ተጠናቋል።

ከመጀመርያ አጋማሽ እንቅስቃሴ ብዙ የተለየ ነገር ባልታየበት ሁለተኛ አጋማሽ መድኖች በጥሩ እንቅስቃሴ ወደ ጎል ቢደርሱም ስህተታቸውን ሳያሻሽሉ በመቅረብ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚያገኙትን ግልፅ የጎል አጋጣሚ ሲያመክኑ ተስተውሏል። በአንፃሩ ኢትዮዽያ ቡናዎች በጠንካራ የአማካይ እና ስል በሆኑ አጥቂዎች በመታገዝ የሚያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም ረገድ ከመድኖች የተሻሉ ነበሩ። ወደ ጨዋታው መገባደጃ የኢትዮዽያ ቡናው አጥቂ ተገኝ ዘውዱ ለቡድኑ ሦስተኛ ለራሱ ሁለተኛ ጎል በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ ጨዋታው በኢትዮዽያ ቡና 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።

በዕለቱ በኢትዮዽያ ቡና በኩል አማካዩ ነብዩ ዳዊት በኢትዮዽያ መድን በኩል አጥቂው ግሩም ኃ/ማርያም ለወደፊት ተስፋ የሚጣልባቸው ተጫዋቾች መሆናቸውን ያሳዩበትን መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል። በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ 05:00 ላይ በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ በተካሄደው የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ አካዳሚዎች 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፈው መውጣት ችለዋል። ነገ በዚህ ምድብ አንድ ጨዋታ ሲካሄድ አፍሮ ፅዮን ከ ወላይታ ድቻ 04:00 ላይ ይጫወታሉ።

በምድብ ሀ ጎፋ ሜዳ በ09:00 ላይ በተደረገ ጨዋታ ማራቶን ደደቢትን 2-0 ሲያሸንፍ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ኢትዮ ኤሌትሪክን 4-2 አሸንፏል። ከዚህ ምድብ አንድ ጨዋታ ነገ ይቀጥልና አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ 09:00 ላይ የሚጫወቱ ይሆናል ።