ከፍተኛ ሊግ ለ | ሀላባ ከተማ ተከታዩ ደቡብ ፖሊስን አሸንፎ መሪነቱን አጠናክሯል

የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ መደረግ ሲጀምሩ ሀላባ ከተማ የቅርብ ተፎካካሪውን በመርታት መሪነቱን አጠናክሯል። ሁለት ጨዋታዎች በዝናብ ምክንያት የተስጓጎሉበት እለት ሆኖም አልፏል።

ሀላባ ላይ በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ሀላባ ከተማ ደቡብ ፖሊስን 2-0 አሸንፏል። በርከት ያሉ የሀላባ አመራሮች እንዲሁም የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ በተከታተሉት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት የመረጡት ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ ክልል ለመድረስ ሲቸገሩ ተስተውሏል። በቀደሙት 15 ደቂቃዎች ተጭነው መጫወት የቻሉት ሀላባ ከተማዎች በአቦነህ ገነቱ እና በስንታየው መንግስቱ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። የጨዋታም ሆነ የግብ ሙከራ ብልጫ የተወሰደባቸው ደቡብ ፖሊሶች ቢኒያም አድማሱ እና አበባየው ዮሐንስ ወደፊት ኳስን ይዞ በመጠጋት በነበራቸው ሚና እንዲሁም ደግሞ ከመቐለ የተቀነሰው ዱላ ሙላቱ በሚደረገው የግራ መስመር እንቅስቃሴ የተፈጠረባቸውን ጫና ማርገብ ችለዋል። በ20ኛው ደቂቃ ከአባባየው ዮሐንስ የተሻገረትን ኳስ ወደግብነት መለወጥ የሚችልበትን አጋጣሚ አግኝተው የነበረ ቢሆንም በግቡ አናት ወጥታለች። በመልሶ ማጥቃት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ደቡብ ፖሊሶች በ34ኛው ደቂቃ ዱላ ሙላቱ በረጅሙ የታሸገረትን ኳስ ከሀላባ ተከላካዮች ሾልኮ በመውጣት ያገኘውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። እምብዛም የግብ ዕድል ባልተፈጠረበት በዚሁ አጋማሽ 38ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየው መንግስቱ ካኋላ የተከላካይ መስመር በረጅሙ የተሻገረትን ኳስ ተቋጣጥሮ ወደፊት ቢገፋውም ግብ ጠባቂው መኳንንት አሸናፊ በፍጥነት በመውጣት አድኖበታል። በተደጋጋሚ ወደፊት የሚጣሉትን ኳሶች በእግሩ እና በግንባሩ በመጠቀም ሲያድን የነበረው የደቡብ ፖሊስ ግብ ጠባቂ መኳንንት አሸናፊ ከተከላካዮቹ ጀርባ ያለውን ቦታ በአግባቡ በመሸፈን ከግብ ጠባቂነት ሚናው ተጨማሪ እገዛ ሲያደርግ ታይቷል

ከዕረፍት መልስ ሀላባ ከተማ ግብ ፍለጋ ረጃጅም ሆነ አጫጭር ኳሶችን ሲጠቀም የነበረ ሲሆን በአንፃሩ ተጋጣሚያቸው ደቡብ ፖሊስ መከላከል ላይ በማመዘን እና ረጃጅም ኳሶችን ወደፊት በመጣል ተጋጣሚያቸውን ፈትነዋል። በ50ኛው ደቂቃ አባባየው ዮሐንስ በግምት 20ሜትር ላይ አክርሮ የመምታት ኳስ የግቡን አናት ጨርፋ ወጥታበታለች። በድጋሚ በ60ኛው ደቂቃ ኤሪክ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ግብጠባቂው አድኖበታል። በተቃራኒው ሀላባ ከተማዋች እስከ 70ኛው ደቂቃ የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ የቀሩ ሲሆን በ70ኛው ደቂቃ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ስንታየው ሽብሩ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው አድኖበታል። በ77ኛው ደቂቃ የደቡብ ፖሊሱ በኃይሉ ወገኔ ያገኘውን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ሲቀር በሀላባ ከተማ በኩል በ79ኛው ደቂቃ ስንታየው መንግስቱ በረጅሙ የተሻገረረትን ኳስ ግብ ጠባቂውን በማለፍ ወደግብነት ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ በግቡ አናት ልኮታል። ሆኖም 89ኛው ደቂቃ ላይ ከተከላካይ ክፍል በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ የመጨረሻውን 10 ደቂቃ ወደ ኃላ ማፈግፈግ ምርጫቸው ያደረጉት ደቡብ ፖሊሶች ከግብ ጠባቂው ባለመናበብ የፈጠሩትን ስህተት ተጠቅሞ ስንታየው መንግስቱ ወደ ግብነት ለውጦ ሀላባዋችን ጮቤ አስርግጧል። በተጫማሪው ደቂቃ ደግሞ ከወልቂጢ ከተማ የተዘዋወረው መሐመድ ናስር ከማዕዘን ምት ከተሻገረው ኳስ ሁለተኛ ግብ ማከል ችሏል። በዚህ መልኩ በሀላባ 2-0 አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታም ሀላባ ከተማ የምድብ ለ መሪነቱን ማጠናከር ችሏል።

በሌሎች ጨዋታዎች ቤንች ማጂን ከስልጤ ወራቤ ያገናኘው ጨዋታ በስልጤ ወራቤ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በሜዳው ያለመሸነፍ ሪከርድ ያለው ቤንች ማጂዎች በጃፋረ ከበደ ጎለ ቢመሩም ስልጤ ወራቤዎች በ38ኛው ደቂቃ የአክሊሉ ተረቀኝ እና በ60ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት በተቆጠረ የገብረ መስቀል ዱባላ ጎሎች አሸናፊ ሆነዋል። በውጤት ቀውስ ውስጥ ያለው ሻሸመኔ ከተማ በድጋሚ አቻ ወጥቷል። ከነገሌ ከተማ ጋር ጨዋታውን ያደረገው ሻሸመኔ ከተማ በ38ኛው ደቂቃ ላይ በተቆጠረው የይድነቃቸው ብርሃኑ ጎል ነጥብ ይጋራ እንጂ በአለማየው ሞላ የ3ኛው ደቂቃ ጎል ቀዳሚ መሆን ችለው የነበሩት ነገሌ ከተማዎች ነበሩ። ጨዋታውም በሙሉ ክፍለ ጊዜ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ፖሊስ ሌላው የከተማው ቡድን ናሽናል ሴሜንትን ገጥሞ 4-2 በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው የራቀበትን ድል አስመዝግቧል።

የተቋረጡ ጨዋታዎች…

ዲላ መቂ 1-0 መቂ ከተማ

በዕለቱ በጣለው ዝናብ በ56ኛው ደቂቃ ላይ የተቋረጠው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ዲላ ከተማ በ44ኛው ደቂቃ በሣሙኤል ቦጋለ ግብ 1-0 እየመራ ነበር። ጨዋታውም ዛሬ 04:00 ላይ እንዲቀጥል ቀጥሮ ተይዞለታል።

ቡታጅራ ከ ሀምበሪቾ

ጨዋታው ከጅምሩ ያልተደረገ ሲሆን ዛሬ 04:00 እንደሚካሄድ ይጠበቃል። ምክንያቱ ደግሞ የቡታጅራ ሜዳ በጎርፍ መጎዳቱ ሲሆን ሁለተኛው አማራጭ ሜዳ አጥር የሌለው በመሆኑ ጨዋታውን በይደር መያዙ ግዴታ ሆኗል።


ቀጣይ የምድብ ለ ጨዋታዎች

ሰኞ ግንቦት 13 ቀን 2010
ቡታጅራ ከተማ 04:00 ሀምበሪቾ
ተቋ ዲላ ከተማ 1-0 መቂ ከተማ
44′ ሳሙኤል ቦጋለ
*56ኛ ደቂቃ ላይ ከተቋረጠበት 04:00 ላይ ይቀጥላል።
ሀዲያ ሆሳዕና 09:00 ካፋ ቡና
ማክሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2010
ወልቂጤ ከተማ 09:00 ጅማ አባ ቡና