የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ 2-3 አልጄሪያ

ጋና ለምታስተናግደው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የመጨረሻ ማጣሪያ ዙር ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአልጄሪያ በአጠቃላይ ውጤት 6-3 ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሆኗል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ሃገራት ብሄራዊ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ – ኢትዮጵያ

በተቻለን መጠን አጥቅቶ የሚጫወት ቡድን ይዘን ለመግባት ሞክረናል፡፡ በማጥቃቱ ሂደት ላይ የተወሰኑ ስህተቶች ስለነበሩ እና በመልሶ ማጥቃት ጎሎች ስለገቡብን የምንነሳበት እድል አልነበረም፡፡ ለሁለተኛው ጎል ስንሄድ ደግሞ ሌላ ጎል ተቆጠረ ስለዚህ ቡድናችን እየወረደ ነው የሄደው፡፡ በአጠቃላይ ግን ሲታይ በነበረው እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ፡፡

የመጀመሪያውን 11 ስናስገባ አስበንበት እና ለምንፈልገው አጨዋወት ይሆናሉ ብለን የምናስባቸውን ነው፡፡ የመጀመሪያው ስላልሰራ ሁለተኛ እቅድ በተቻለን መጠን ተጠቅመናል፡፡ በተቻለን መጠን በነበረው ሰዓትም ለመጠቀም ሞክረናል፡፡ ያው ውጤቱ እንደታየው ሆኗል ማለት ነው፡፡

ተጋጣሚዎቼ እዚህ ሲመጡ የመጀመሪያ አማራጫቸው መከላከል እንደሆነ ያስታውቃል። ግን እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት እያጠቁን ስለነበረ በፈጠርነው ስህተት ተጠቅመው ግቦችን ማግባት ችለዋል፡፡ በጣም ጠንካራ ጎናቸው ይሄ ነው፡፡

ከገቡት 11 ተጫዋቾች መካከል ሁለቱ ብቻ ናቸው የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ ያላቸው፡፡ እንደኔ ያደረኩት አስቤበት እና ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብዬ ነው፡፡ አሁንም ደግሞ ለሆነው ነገር ሁሉ ሃላፊነት እወስዳለው፡፡ ከዚህ በኃላ ይሄን ነገር ተረክቦ የሚያስኬደው አካል እንግዲህ እድለኛ ነው ወይም ደግሞ ጥሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ይኖረናል ማለት ነው፡፡ እኔ ለሃገሬ የሚጠቅመውን አድርጌያለው ለእሱም ሃላፊነቱን እወስዳለው፡፡

አሰልጣኝ አዘዲን ቺ – አልጄርያ

በጣም ደስተኛ ነኝ ምክንያቱም ዋነኛ አላማችን ወደ ጋና ማምራት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ጥሩ ነው፡፡ ለወደፊቱ መልካሙን ሁሉ እመላቸዋለው፡፡

ጨዋታው መልካም ነበር፡፡ የገረመኝ ነገር በስታዲየሙ የተገኘው ደጋፊ ነው፡፡ ደጋፊዎቹ ሃገራቸውን ሲደግፉ ማየት ደስ ይላል፡፡ ግብ ስላስቆጠርን እንጂ በእንቅስቃሴ ኢትዮጵያ የበላይ ነበረች፡፡ በእንቅስቃሴው ተጋጣሚያችን ማሸነፍ ይገባው ነበር። ሆኖም እኛ ግብ በማስቆጠራችን ለአፍሪካው ዋንጫ በቅተናል፡፡