የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 20ኛ ሳምንት (ምድብ ለ)

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት እና ዛሬ ሲካሄዱ መሪው ደቡብ ፖሊስ እንዲሁም ተከታዮቹ ሀላባ እና ዲላ አሸንፈዋል። 

የምድቡ መሪ ደቡብ ፖሊስ ሀዋሳ ላይ ቡታጅራ ከተማን አስተናግዶ በኬንያዊው አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳ ብቸኛ ጎል 1-0 አሸንፏል። በዚህም የምድቡን መሪነት ይዞ መዝለቅ ችሏል። ወደ ወራቤ ያቀናው ተከታዩ ሀላባ ከተማም ስንታየሁ ሽብሩ ባስቆጠረው ጎል በተመሳሳይ ውጤት 1-0 ሲያሸንፍ ከደቡብ ፖሊስ ያለውን የአንድ ነጥብ ልዩነት አስጠብቆ ማስቀጠል ችሏል።

ጅማ አባ ቡና በሜዳው ናሽናል ሴሜንትን አስተናግዶ 3-3 በሆነ ቻ ውጤት ተለያይቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ግዜ አሰልቺ የሜዳ ላይ እቅስቃሴ የታየበት እንዲሁም የባለሜዳዎቹ ደጋፊዎችን ያበሳጨ እና ቅሬታዎችንም በቡድኑ ላይ ያሰሙበት ነበር። የመጀመርያ ኢላማውን የጠበቀ የጎል ሙከራ በሀይደር ሸረፋ በ23ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመተውን ሀምዲ ቶፊቅ እንደምንም አውጥቶበታል። 41ኛው ዳዊት ተሾመ ናሽናሎችን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ሲችል በድጋሚ በ43ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ዳዊት ተሾመ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ልዩነቱን ወደ ሁለት አሰፋ ተብሎ ሲጠበቅ በግቡ አናት ላይ ሰዶታል። ይሄው ኳስ በመልስ ምት ሲጀመር ብዙዓየሁ እንደሻው ጋር ደርሶ እረፍት ከመውጣታቸው በፊት በ44ኛው ደቂቃ ቡድኑን አቻ አድርጎ ለእረፍት ወጥተዋል።

ከእረፍት መልስ ጨዋታው በፈጣን እቅስቃሴና በጎል ሙከራዎች ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ  ነበር። በ51ኛው ደቂቃ ሂደር ሙስጠፍ ከማእዘን የተሻገረውን በግንባሩ በመግጨት አባቡናን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ናሽናሎችን አቻነት ግብ ዳዊት ተሾመ ሲያስቆጥር በ73ኛው ደቂቃ የናሽናል ሴሜንት አምበል የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ከመሀል ዳኛው ጋር በገባው ሰጣገባ በቀይ ካርድ ወጥቷል። በአስር ተጫዋቾች የተጫወቱት ናሽናሎች በ84ኛው ደቂቃ ቢኒያም ጥዑመልሳን በግሩም ሁኔታ ከመሀል ሜዳ ከርቀት አስቆጥሮ ሶስት ለሁለት መምራት ቢችሉም ብዙዓየሁ እንደሻው በ87ኛው ደቂቃ አባቡናዎችን በሜዳቸው ከመሸነፍ ያዳናቸውን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 3ለ3 ተጠናቋል።

ዲላ ከተማ ሻሸመኔን በሳሙኤል በቀለ እና ሐብታሙ ፍቃዱ ግቦች 2-0 በማሸነፍ ወደ ሶስተኛ ደረጀ ከፍ ሲል ሀምበሪቾ ከተማ በቴዲ ታደሰ ብቸኛ ጎል ቤንጅ ማጂ ቡናን 1-0 አሸንፏል። ነገሌ ከተማ ደግሞ በወልቂጤ ከተማ በሜዳው የሁለት ለ አንድ ሽንፈት አስተናግዷል።

መቂ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ያለምንም ግብ ሲጠናቀቅ ወደ ዛሬ ተሸጋግሮ የተደረገው የካፋ ቡና እና የድሬዳዋ ፖሊስ ጨዋታ በተመሳሳይ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።