ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ከተማ ከሜዳው ውጪ አዳማን አሸንፏል

በሉሲዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ምክንያት ለ45 ቀናት ያህል ተቋርጦ የቀሰየው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን ዛሬ በተደረገ አንድ የ13ኛ ሳምንት ጨዋታ ሲጀመር ሀዋሳ ከተማ ከሜዳው ውጪ አዳማ ከተማን 3-0 አሸንፏል።

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም 09:00 ላይ በጀመረው ጨዋታ በሁለተኛው ዙር አቋማቸውን አሻሽለው የቀረቡት ሀዋሳ ከተማዎች ያገኙትን የጎል አጋጣሚዎች በመጠቀምና የመሀል ክፍሉን በመቆጣጠር በአዳማ ላይ የበላይ መሆን ችለዋል። ብዙም የጎል ሙከራ ባልተደረገበት የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በ21ኛው ደቂቃ የአዳማ ግብ ጠባቂ እምወድሽ እና ተከላካይዋ ባንቺአየው ታደሰ መካከል በተፈጠረው አለመናበብ ከጀርባቸው አምልጣ የገባችው ምርቃት ፈለቀ ጎል አስቆጥራ ሀዋሳዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች። አዳማዎች እንደ ቡድን ኳሱን አደራጅቶ ወደ ፊት ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት መልካም ቢባልም የሜዳው ሦስተኛ ክፍል ሲደርሱ ኳሱ እየተበላሸ ለማግባት የሚያደርጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። አጥቂዋ ሴናፍ ዋቁማ በግሏ የጎል አጋጣሚ ለመፍጠር ብትሞክርም ጥረቷ ሳይሳካ ቀርቷል። 35ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ትንቀሳቀስ የነበረችው እታለም አመኑ ከሳጥን ውጭ ጥሩ አድርጋ የመታችው ኳስ ለጥቂት በግቡ አናት ሲወጣ የመጀመርያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ በጥሩ መንገድ ያቀበለቻትን ኳስ ልደት ቶሎዓ ገፍታ በመግበት በጥሩ ሁኔታ በማስቆጠር የሀዋሳን የግብ መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጋ ለእረፍት ወጥተዋል ።

በሁለተኛው አጋማሽ ገና በተጀመረ በ47ኛው ደቂቃ ላይ እታለም አመኑ በጨዋታ እንቅስቃሴ ከ30 ሜትር ርቀት በጥሩ ሁኔታ በመምታት ያስቆጠረችው ጎል የሀዋሳን የግብ መጠን ወደ ሦስት ከፍ ሲያደርግ የአዳማዎችን ወደ ጨዋታው ለመመለስ የነበራቸውን ፍላጎት አቀዝቅዞታል። ከመጀመርያው አጋማሽ ብዙም ተለውጠው ያልመጡት አዳማዎች ብዙም የረባ ሙከራ ባያደርጉም ተቀይራ የገባችው አጥቂዋ ይታገሱ ተ/ወርቅ በሁለት አጋጣሚዎች አክርራ የመታቻቸውን ኳሶች የሀዋሳዋ ግብ ጠባቂ አባይነሽ ኤርቄሎ ያደነችባት፣ 83ኛው ደቂቃ ሴናፍ ዋቁማ ወደ ጎል ሞክራ በድጋሚ በድጋሚ አባይነሽ ያዳነችው አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበር። በሀዋሳ በኩል በሁለቱ አጥቂዎች ልደት ተሎዓ እና ምርቃት ፈለቀ አማካኝነት የሚፈጥሩት የማጥቃት እንቅስቃሴ ለአዳማ ተከላካዮች ፈታኝ የነበረ ሲሆን 73ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ ብቻዋን ከግብ ጠባቂዋ ጋር ተገናኝታ ያልተጠቀመችበት የሚጠቀስ ሙከራ ነው። ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት አሰልጣኝ ዮሴፍ የመረጡት የጥንቃቄ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ተሳክቶላቸው ሀዋሳዎች ከጨዋታው የሚፈልጉትን ሦስት ነጥብ አሳክተው ወጥተዋል።