ኢትዮጵያ ቡና የተስተካካይ መርሀ ግብርን ለመቀበል እንደሚቸገር አስታወቀ

በ25ኛው እና 27ኛው ሳምንት ሳይካሄዱ የቀሩትን ሶስት ጨዋታዎች ለማከናወን የወጣው መርሀ ግብር ከኢትዮጵያ ቡና በኩል ተቃውሞ ገጥሞታል።

ኢትዮጵያ ቡና በይፋዊ የፌስ ቡክ ገፁ ባስነበበው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተላከ ደብዳቤ በመጪው ሰኞ ከሀዋሳ ከተማ ጋር እንዲያደርገው ቀን የተቆረጠለት ጨዋታ ላይ ነው ቅሬታውን ያሰማው። ከነገ በስትያ አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማን በኢትዮጵያ ዋንጫ የሚገጥመው ክለቡ ከአራት ቀናት በኃላ ከሀዋሳ ከተማ ጋር በተስተካካዩ የሊግ መርሀ ግብር እንዲጫወት መደረጉ አግባብ አለመሆኑን አስረድቷል። ቡድኑ ከሐሙሱ የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ በኋላ አርብ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ በድጋሜ ደግሞ ለሰኞው ጨዋታ ቅዳሜ ወደ ሀዋሳ መጓዙ ለድካም የሚዳርገው እና በውጤቱ ላይም ተፅዕኖ እንደሚኖረው በደብዳቤው አስታውቋል።

እንደ ክለቡ ሀሳብ ከሆነ በሁለቱ ጨዋታዎች መካከል እረፍት እና ልምምድ ለማድረግ የማያስችል የጊዜ ልዩነት ባለመኖሩ መርሀግብሩን ለመቀበል እንደሚቸገር ገልጿል።