አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እና ፋሲል ከተማ ተለያዩ

ያለፉትን 4 ወራት በፋሲል ከተማ የቆዩት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከክለቡ ጋር ተለያይተዋል።

በ19ኛው ሳምንት ወልድያ ላይ ወልድያን በመርታት የመጀመርያ ጨዋታቸውን በድል የጀመሩት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ያለፉትን አራት ወራት ከፋሲል ከነማ ጋር በቆዩበት ጊዜያት ካደረጓቸው 12 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ውስጥ አራት ጨዋታ  አሸንፈው በአራቱ ጨዋታ ሽንፈት አስተናግደው በአራት ጨዋታ አቻ በመለያየት በ41 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከፋሲል ከተማ ጋር የነበራቸው ኮንትራት መፈፀሙ የመለያየታቸው ምክንያት እንደሆነ ገልፀው ከፋሲል ጋር በነበራቸው መልካም ቆይታ የክለቡን አመራሮች እንዲሁም ደጋፊዎችን አመሰግነዋል። በቀጣይም ክለቡ መልካም ጊዜ እንዲገጥመው በመመኘት ቀጣይ ማረፊያቸው ወደፊት እንደሚታወቅ ገልፀዋል።

ፋሲል ከተማ አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ እና ምክትሉን ተገኝ እቁባይ ማሰናበቱ ተከትሎ የቀድሞ የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቀጣዩ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ እንዲሆኑ መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ መቅጠራቸው ይታወቃል።