ሊዲያ ታፈሰ በዓለም ዋንጫው የመጀመሪያ ጨዋታዋን በዋና ዳኝነት መራች

በፈረንሳይ አስተናጋጅነት እየተከናወነ የሚገኘው ከ20 ዓመት በታች የአለም ዋንጫ በ16 ሃገራት መካከል እየተደረገ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ በውድድሩ ባትሳተፍም ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ግን በዳኝነት ተሳታፊ ሆናለች።

ከነሃሴ 5 እስከ 24 እየተደረገ በሚገኘው በዚህ ውድድር አፍሪካን በመወከል ስድስት ዋና እና ረዳት ዳኞች በድምሩ ተሳታፊ ሲሆኑ ከኢትዮጵያ ያመራችው ሊዲያ ትላንት ምሽት የውድድሩ አስተናጋጅ ፈረንሳይ እና ኒውዝላንድ ያረጉትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት መርታለች። ጨዋታው ያለ ግብ ሲጠናቀቅ በውድድሩ የመጀመሪያው ያለ ግብ የተጠናቀቀ የአቻ ውጤት ሆኖም ተመዝግቧል። ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊድያ ታፈሰ የትላንትናው ጨዋታ ለዋና ዳኝነት የመጀመሪያዋ ይሁን እንጂ ከሶስት ቀናት በፊት ጃፓን አሜሪካን አንድ ለምንም ስታሸንፍ በአራተኛ ዳኝነት ጨዋታውን መምራቷ ይታወሳል።

16 ሃገራት በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር የምድብ ጨዋታዎች አለመጠናቀቃቸው እና ገና የግማሽ፣ የሩብ እንዲሁም የፍፃሜ ጨዋታዎች ስለሚቀሩ ሊድያ ሌሎች ጨዋታዎችን የመምራት እድል እንደምታገኝ ይገመታል።

በውድድሩ አፍሪካ በጋና እና ናይጄሪያ የተወከለች ሲሆን በምድብ ሀ ከአስተናጋጇ ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድ እና ኒውዝላንድ ጋር የተደለደለችው ጋና በተጫወተቻቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት አራት ጎሎች ተቆጥረውባት ገና አንድ ቀሪ ጨዋታ እያላት ያለ ምንም ነጥብ ከወዲሁ ከውድድሩ ተሰናብታለች። በምድብ መ የምትገኘው ናይጄሪያ ደግሞ በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ በጀርመን አንድ ለምንም ተሸንፋ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች እያሏት የምድቡ ግርጌ ላይ ተቀምጣለች።

ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ከዚህ ቀደም የተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን መምራቷ የሚታወስ ሲሆን በ2016 ጆርዳን ላይ የተደረገው ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ዳኛዋ በአለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ከመራቻቸው ጨዋታዎች የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።