ደደቢት ተጨዋቾች ማስፈረም ጀምሯል

ባሳለፍነው ወር ከቀደመው የዝውውር አካሄዱ በተለየ መንገድ እንደሚቀጥል ይፋ ያደረገው ደደቢት እስካሁን ለዓመታት አብረውት የቆዩትን ተጨዋቾቹን ከመሸኘት በቀር ምትኮቻቸውን ለማምጣት የማስፈረም እንቅስቃሴ ሳያደርግ ቆይቷል። ከሌሎቹ ክለቦች አንፃር በዝቅተኛ ደሞዝ የሚጫወቱ ፈራሚዎችን ብቻ እንደሚፈልግ ገልፆ የነበረው ክለቡ በዕቅዱ መሰረት ከሳምንቱ መጨረሻ ጀምሮ ከ7 በላይ ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

እንዳለ ከበደ ወደ ደደቢት ካመሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። የመስመር አጥቂው ዓመቱን ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ባረጋገጠው ባህር ዳር ከተማ ያሳለፈ ሲሆን በዘንድሮ ቆይታው አራት ግቦችን ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።

አዳማ ላይ በተካሄደው የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ላይ ምልመላ ሲያከናውን የቆየው ደደቢት ዓይኑ ያረፈባቸው ሶስት የሺንሺቾ ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል። ተመስገን በጅሮንድ ሀምበሪቾን ለቆ ሺንሺቾን የተቀላቀለው ዘንድሮ ሲሆን የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ነው። ዳግማዊ ዓባይ ከሶዶ ከተማ ወደ ሺንሺቾ ካመራ በኋላ ከቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቸች አንዱ ከመሆኑ ባሻገር በቀኝ ተከላካይ እና በመሀል ተከላካይ ስፍራ ላይ ቡድኑን አገልግሏል። ሌላው ለክለቡ የፈረመው ጥዑመልሳን ኃይለሚካኤል ከወላይታ ድቻ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ክለቡን የተቀላቀለው ዘንድሮ ሲሆን የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ነው።

ክለቡ ከአራቱ በተጨማሪ ሌሎች ተጫዋቾች ከከፍተኛ ሊግ ያስፈረመ ቢሆንም በሳምንቱ መጨረሻ ወሳኝ ጨዋታዎች ያሉባቸው በመሆኑ ይፋ አልተደረጉም። ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮም ይፋ ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ደደቢት ከአዳዲስ ተጫዋቾች ዝውውር ባሻገር ነባር ተጫዋቾችን ኮንትራት ለማራዘም ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆን ዓለምአንተ ካሳ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ውሉን ያራዘመ ተጫዋች ነው።

ፎቶ ከግራ ወደ ቀኝ – እንዳለ ከበደ፣ ጥዑመልሳን ኃይለሚካኤል፣ ዳግማዊ ዓባይ፣ ተመስገን በጅሮንድ