ሴቶች ዝውውር | ንግድ ባንክ አምስት ተጫዋቾች ሲያስፈርም የሰባት ተጫዋቾችን ውል አድሷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግን በ2ኛነት ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ዝውውር እንቅስቃሴ በመግባት አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

በደደቢት ጥሩ ዓመት ያሳለፉት አማካይዋ ትዕግስት ዘውዴ እና አጥቂዋ ሰናይት ባሩዳ፣ በጌዴኦ ዲላ በምታሳየው ብቃት እስከ ብሔራዊ ቡድን የደረሰችው ተከላካይዋ ገነሜ ወርቁ፣ ደደቢትን ለቃ ዓመቱን በድሬዳዋ ከተማ ያሳለፈችው ግብ ጠባቂዋ ፍሬወይኒ ገብረመስቀል አረንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊስ አማካይ የነበረችው ኪፊያ አብዱራህማን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሁለት ዓመታት ለመጫወት ተስማምተው ክለቡን የተቀላለቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ንግድ ባንክ ከአዳዲስ ተጫዋቾች ፊርማ በተጨማሪ የሰባት ነባር ተጫዋቾቹን ፊርማ አድሷል። ግብ ጠባቂዋ እየሩሳሌም፣ ተከላካዮቹ አዳነች ጌታቸው፣ ታሪኳ ደቢሶ እና ጥሩአንቺ መንገሻ፣ አማካዮቹ ትዕግስት ያደታ፣ ቤተልሄም እና ዙለይካ ጁሀድ ውላቸው በአንድ ዓመት ተራዝሟል።