ካሜሩን 2019 | ኢትዮጵያ ጋናን በአዲስ አበባ ስታዲየም ትገጥማለች

በ2019 በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ በማጣሪያ ላይ ተካፋይ እየሆነች የምትገኘው ኢትዮጵያ በምድቡ አምስተኛ ጨዋታ ጋናን ትገጥማለች። ዋሊያዎቹ የደበዘዘ የማለፍ ተስፋቸውን ለማለምለም እጅግ ወሳኝ የሆነው ጨዋታን የሚያከናውኑት በአዲስ አበባ ስታድየም ኅዳር 9 ነው።

የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ መሪነት የ5-0 ሰፊ ውጤት ከተረታ በኃላ በአዲሱ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ መሪነት በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም ሴራሊዮንን ገጥሞ በጌታነህ ከበደ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት የረታው ብሔራዊ ቡድኑ ጥቅምት 30 በባህር ዳሩ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ኬኒያን ቢያስተናግድም ያለምንም ግብ አጠናቆ ከሶስት ቀናት በኋላ ካሳራኒ ላይ 3-0 በሆነ ውጤት ተሸንፎ የማለፍ ተስፋው ደብዝዞ ጋናን ያስተናግዳል። ብሔራዊ ቡድኑ ይህንን ጨዋታ ዳግም በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያደርጋል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም የአዲስ አበባ ከፍታን ተጠቅሞ ውጤታማ ለመሆን ሲባል ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም መዞሩን ሶከር ኢትዮጵያ ከፌድሬሽኑ ያገኘችሁ መረጃ ይጠቁማል፡፡

አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ቀደም ብለው ሴራሊዮን እና ኬኒያን በገጠሙበት ጨዋታ ላይ ራሳቸው ያልመረጧቸው ተጫዋቾች በአብዛኛው ተካተው የነበሩ ሲሆን አሁን ደግሞ አሰልጣኙ ፕሪምየር ሊጉ በመጀመሩ ምክንያት ከረዳቶቻቸው ጋር በመሆን መምረጥ ጀምረዋል። አሰልጣኝ አብርሀም ወደ መቐለ አምርተው የመቐለ እና የደደቢት፣ ረዳታቸው ሙሉጌታ ምህረት የሲዳማ እና ፋሲልን እንዲሁም የሀዋሳ እና የወልዋሎን፤ ሌላው ረዳት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ኢትዮጵያ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማን፣ የግብ ጠባቂዎቹ አሰልጣኝ ውብሸት ደሳለኝ ደግሞ የአዳማ እና ጅማ አባ ጅፋርን ጨዋታ የተመለከቱ ሲሆን በነገው ዕለት የተመረጡ ተጫዋቾች ዝርዝር ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል። ጥቅምት 26 ዝግጅት የሚጀምሩ ሲሆን ጥቅምት 30 ይደረጋሉ ተብለው የሚጠበቁ የ2ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መደረጋቸውም አጠራጣሪ ሆኗል።