ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለ ዋና አሰልጣኝ ባህር ዳር ያለ ውጪ ተጫዋቾቹ ይገናኛሉ

እሁድ በአዲስ አበባ ስታድየም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ የዓመቱ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ሆኖም ከአንደኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች መካከል አንዱ በሆነው በዚህ ጨዋታ ከሁለቱም ክለቦች የማንመለከታቸው የቡድን አባላት ይኖራሉ።

ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶን የአንድ ዓመት ኮንትራት እየቀራቸው ያሰናበተው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣይ ቡድኑን ተረክበው የሚመሩትን ዋና አሰልጣኝ ለመቅጠር ሲያጠና ቆይቶ የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው አሰልጣኝን አነጋግሮ እንደጨረሰ እና በቅርቡም ቡድኑን ይረከባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ እየተነገር ይገኛል። ነገር ግን አንዳንድ ያላለቁ ጉዳዮች በመኖራቸው ምክንያት ቅዱስ ጊዮርጊስ በዕሁዱ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታ ሰኞ እንደሚገቡ ከሚጠበቁት ዋና አሰልጣኙ ውጪ በምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ እየተመራ ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል።

አዲስ አዳጊው ባህር ዳር ከተማ ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ በሚኖረው ተሳትፎ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረሙ ይታወቃል። ከቀናት በፊት በተዘጋው የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮትም ሀሪስተን ሄሱ (ግብ ጠባቂ ከኢትዮጵያ ቡና) ፣ ጃኮ አራፋት (መሀል አጥቂ ከወላይታ ድቻ) ፣ አሌክስ አሙዙ (የመሀል ተከላካይ ከአርባምንጭ ከተማ) ፣ አህመድ ዋቴራ (የአጥቂ መስመር ተጫዋች ከአይቮሪኮስታዊ) ማስፈረሙ ይታወሳል። ሆኖም አራቱ ተጫዋቾች ለእሁዱ ጨዋታ እንደማይደርሱ ተረጋግጧል። ሁለቱ ተጫዋቾች ቀድሞ የነበሩበት ክለቦች የመልቀቂያ ወረቀት አለማግኘታቸው እና የተቀሩት ደግሞ የመኖርያ ፍቃዳቸው ጉዳይ አለመጠናቀቁ ለጊዮርጊሱ ጨዋታ ያለመድረሳቸው ምክንያቶች ሆነዋል።

ክለቦች ከፍተኛ ገንዘብ እያወጡ የሚያስፈርሟቸው የውጭ ዜግነት ያላቸው ተጨዋቾች ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጫወት የሚያስፈልገውን ፍቃድ እንዲያገኙ ትኩረት ሰጥቶ የሚያስፈፅም አካል ባለመኖሩ ምክንያት ባለፈው ሳምንት በተካሄዱ የሊጉ የመጀመርያ አምስት ጨዋታዎች የውጭ ሀገር ተጫዋቾች ያለተሳተፉባቸው አጋጣሚዎች ተስተውለዋል።