ኢትዮጵያ እና ጋና የመጨረሻ ልምምዳቸውን ሰርተዋል

በዮናታን ሙሉጌታ እና ተሾመ ፋንታሁን

የኢትዮጵያ እና የጋና ብሔራዊ ቡድኖች በ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የሚያደርጋቸውን ውጤት ለማግኘት አምስተኛ የምድብ ጨዋታቸውን ነገ በአዲስ አበባ ስታድየም 10፡00 ላይ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ከወሳኙ ጨዋታ በፊትም ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ ጨዋታውን በሚያደርጉበት የመዲናዋ ስታድየም የመጨረሻ ልምምዳቸውን አድርገዋል።

ረፋድ 04፡00 ላይ ልምምዱን በመስራት ቀዳሚ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነበር። ቡድኑ ሃያ አምስት ተጫዋቾቹን በመያዝ ቀለል ያሉ ልምምዶችን ሰርቷል። በዚሁ የመጨረሻ የልምምድ መርሀ ግብር ላይም የቡድኑ አባላት ጥሩ መንፈስ ላይ እንደሚገኙ በግልፅ ይታይ ነበር። ከዋልያዎቹ ስብስብ መሀል ጌታነህ ከበደ እና አምሳሉ ጥላሁን ጉዳት ላይ የሚገኙ ሲሆን ለብቻቸው ተነጥለውም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲሰሩ ተስተውሏል። 

ታዋቂ ከዋክብትን የያዘው የጋና ብሔራዊ ቡድን ደግሞ 10፡00 ላይ ከኳስ ጋር እና ያለኳስ ቀለል ያለ ልምምድ ያደረገ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ ከመምጣቱ በፊት የሀገራችንን ከፍታ ለመቋቋም በጎረቤት ሀገር ኬንያ ከሰኞ ጀምሮ ሲዘጋጁ መቆየታቸው ይታወሳል። 

ቡድኑ በዛሬው ልምምዱ ለአፍሪካ ህብረት ስብሰባ አዲስ አበባ በሚገኙት የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ የተጎበኘ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ ለተጫዋቾቻቸው መልካም እድል ተመኝተውላቸዋል። የቡድኑ አምበል አሳሞአ ጅያን በጨዋታው የቻሉትን ሁሉ አድርገው እንደሚያሸንፉም ለፕሬዚዳንት አዶ ቃል ገብቷል። አሳሞአ “ከባለሜዳ ጋር መጫወት ሁልጊዜም ቀላል አይሆንም ከኢትዮጽያም ጋር በደጋፊያቸው ፊት መጫወት ከባድ ነው ይሁን እንጂ ይህን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ ስላለብን የቻልነውን ሁሉ አድርገን እናሸንፋለን።” ብሏል።

በመጨረሻም ጥቋቁር ከዋክብቱ እግዚአብሔር የሚወዳቸው ልጆቹን አይተዋቸውም ከመከራና ከችግር ይታደጋቸዋል የሚል መንፈሳዊ መዝሙር በጋራ ዘምረው የእለቱን የልምምድ መርሃ-ግብር አጠናቀዋል።

ጨዋታው ነገ 10፡00 በአዲስ አበባ ስታድየም ሲካሄድ ከረፋድ 4:00 ጀምሮ የስታድየም በሮች ክፍት እንደሚደረጉ ታውቋል ።

error: Content is protected !!