የ2ኛ ዲቪዝዮን ሁለተኛ ሳምንት – አቃቂ ቃሊቲ እና ሻሸመኔ ሁለተኛ ድላቸውን አስመዝግበዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን የሁለተኛ ሳምንት ዛሬ በተካሄዱ ጨዋታዎች ሲጠናቀቅ አቃቂ ቃሊቲ እና ሻሸመኔ ከተማ ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን ማስመዝገብ ችለዋል። 

ማክሰኞ በተጀመረው የዚህ ሳምንት መርሐ ግብር ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ ቦሌ ክፍለ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በ35ኛው ደቂቃ ላይ ብስራት ጥላሁን ከትዕግስት ዳልጋ የተሻገረላትን ኳስ ተጠቅማ የፋሲልን ብቸኛ የማሸነፍያ ጎል ማስቆጠር ችላለች። ለግቡ መቆጠር ከፍተኛ ሚና የተጫወተችው አማካይዋ ትዕግስት ዳልጋ በደረሳባት ከባድ ጉዳት ወደ ሆስፒታል አምርታ የነበረ ሲሆን በመልካም ጤንነት ላይ እንደምትገኝ ተገልጿል። ፋሲል ከነማ በመጀመርያው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ለመጫወት መርሐ ግብር ወጥቶለት የነበረ ቢሆንም ቡና በውድድሩ እንደማይሳተፍ በመግለፁ ሳይጫወት መቅረቱ ይታወሳል።

ውድድሩ ዛሬ ሲቀጥል 9:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከ ሻሸመኔ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ እስከመጨረሻው ደቂቃ በፉክክር ታጅቦ በእንግዳው ቡድን ሻሸመኔ ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። የመጀመርያውን አጋማሽ በንፋስ ስልክ የግብ ክልል ተጥግተው የተጫወቱት ሻሸመኔዎች በ17ኛው ደቂቃ ዓለሚቱ ዲሪባ ሁለት ተከላካዮችን በማለፍ ባስቆጠረችው ጎል ቀዳሚ ሆነዋል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ብርቄ አማረ ከቅጣት ምት የሞከረችው ኳስ አግዳሚውን ገጭቶ ሲወጣ በ25ኛው ደቂቃ በንፋስ ስልክ የግብ ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ዓለሚቱ ዲሪባ ወደ ግብነት በመለወጥ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ አድርጋ በሻሸመኔ 2-0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ተሻሽለው የገቡት ንፋስ ስልኮች በተደጋጋሚ ወደ ሻሸመኔ የግብ ክልል በመድረስ ሙከራዎች አድርገዋል። በ65ኛው ደቂቃ ማርታ አያናው የመጀመሪያውን ግብ በማስቆጠር የግብ ልዩነቱን ማጥበብ ብትችልም በ77ኛው ደቂቃ ወደ ሜዳ ተቀይራ የገባችው የሻሸመኔዋ ጡባ ናስሮ የግብ ጠባቂ ስህተት ተጠቅማ ግብ በማስቆጠር ልዩነቱን በድጋሚ ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች።

ከጎሉ በኋላም ንፋስ ስልኮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጫና የፈጠሩ ሲሆን ትግዕስት ሽኩር ከርቀት በመምታት ግብ በማስቆጠር ልዩነቱን ማጥበብ ችላለች። በተጨማሪው ደቂቃ በሻሸመኔ የግብ ክልል ኳስ በእጅ ተነክቶ እንዲሁም የንፋስ ስልክ ተጫዋች በተሰራባት ጥፋት ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዳ ወደ ሆስፒታል ብትወሰድም ዳኛው በዝምታ አልፏል በሚል የንፋስ ስልክ አባላት ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ተስተውሏል።
ቀጥሎ የተካሄደው የልደታ ክፍለ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጨዋታ በአቃቂ 2-0 የበላይነት ተጠናቋል። በመጀመርያው አጋማሽ አቃቂ ቃሊቲዎች የተሻሉ የነበሩ ቢሆኑም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከእረፍት በኋላም የተሻሉ የነበሩት አቃቂ ቃሊቲዎች በፍጥነት ባስቆጠሯቸው ጎሎች አሸናፊ መሆን ችለዋል። በ47ኛው ደቂቃ ንግስት ኃይሉ ከሳጥን ውጪ በግሩም ሁኔታ ቀዳሚውን ጎል ስታስቆጥር ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ቤዛዊት ንጉሴ ከመሐል ሜዳ የተሻገረውን ኳስ ከተከላካዮች አምልጣ በመውጣት በጥሩ አጨራረስ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥራለች። ከጎሎቹ በኋላ ልደታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት ቢችሉም ኳስ ከመቆጣጠር ባለፈ የግብ እድሎች መፍጠር ሳይችሉ በመቅረታቸው ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው በአቃቂ ቃሊቲ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው ሳምንት ሰኞ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እንዲሁም ማክሰኞ በመቐለ ሰባ እንደርታ እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል ሊደረጉ የነበሩ ጨዋታዎች አካዳሚ እና ቡና እንደማይሳተፉ በመግለፃቸው ሳይከናወኑ የቀሩ ናቸው።

የደረጃ ሰንጠረዥ፣ የግብ አስቆጣሪዎች ደረጃ እና ቀጣይ ጨዋታዎች ይህንን ይመስላሉ:-