ደቡብ ፖሊስ ከ ፋሲል ከነማ | ቅድመ ዳሰሳ

ዛሬ ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስ እና ፋሲል ከነማ የሚያደርጉትን የአምስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በቅድመ ዳሰሳችን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል። 

የሀዋሳው ሰው ሰራሽ ሜዳ እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም 9፡00 ላይ የአምስተኛ ሳምንት የሊግ ጨዋታ ያስተናግዳል። በዚህ ጨዋታ ደቡብ ፖሊስ በተመሳሳይ እስካሁን ሦስት ጨዋታዎችን ካደረገው ፋሲል ከነማ ጋር ነው የሚገናኘው። ሁለቱ ክለቦች በሚሌኒየሙ መግቢያ ላይ በፕሪምየር ሊጉ ከተገናኙ ከአስራ አንድ ዓመታት በኋላ እርስ በእርስ የሚጫወቱት። ለሦስተኛ ጊዜ በሜዳቸው ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ደቡብ ፖሊሶች ደደቢትን ከረቱበት ውጤት ውጪ ሁለት ጊዜ ሽንፈት ገጥሟቸው 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አፄዎቹም በተመሳሳይ በአንድ ጨዋታ ብቻ ድል የቀናቸው ቢሆንም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ በመጋራቸው ከዛሬው ተጋጣሚያቸው በአንድ ነጥብ ከፍ በማለት 6ኛ ደረጃን እንዲይዙ ሆኗል። 

በሲዳማ ቡና ከተረቱበት ጨዋታ በኋላ በድጋሜ ወደ ሀዋሳ የሚያቀኑት ፋሲል ከነማዎች ለአጨዋወታቸው ምቹ በሆነው ሜዳ ላይ የተለመደው በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ የተመሰረተው አጨዋታቸውን እንደሚተገብሩ ይጠበቃል። ደከም ብሎ የታየው የደቡብ ፖሊስ የግራ መስመር የመከላከል ክፍል ደግሞ ለፋሲሎች የማጥቃት መስመር ተመራጭ ዒላማ ሊሆን የሚችልበት ዕድል ይኖራል። በዚህ ሂደት ውስጥ ሽመክት ጉግሳ ከአበባው ቡታቆ የሚገናኙበት የሜዳ ክፍል ተጠባቂ ይሆናል። ከአጥቂ ክፍላቸው ውስጥ በሁለቱ መስመሮች የተሻለ ጥቃት የሚሰነዝሩት ደቡብ ፖሊሶች በበኩላቸው መስፍን ኪዳኔ እና ብሩክ ኤልያስን በመጠቀም  በፋሲል የመሀል እና የመስመር ተከላካዮች መካከል ለመግባት የሚሞክሩበት ሂደትም ከጨዋታው ይጠበቃል። 

 
ደቡብ ፖሊስ ምንም የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና የሌለበት ሲሆን አማካዩን ኤርሚያስ በላይ ከጉዳት እንዲሁም በቂ ልምምድ ባለመስራቱ ከጨዋታ ርቆ የነበረው ጋናዊው ተከላካይ አዳሙ መሀመድ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል። አጥቂው ፈሲል አስማማውን አሁንም በጉዳት የማያገኙት አፄዎቹ የተከላካዩን ሙጂብ ቃሲምን በጉዳት ምክንያት የመጠቀም እና ያለነጠቀማቸው ነገር አለየለትም። 

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ በፀጋው ሽብሩ ከከፍተኛ ሊግ በማደግ ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሪሚየር ሊጉ ይህን ጨዋታ እንዲመራ ተመድቧል። 

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

ፍሬው ጌታሁን

ዘነበ ከድር – ዘሪሁን አንሸቦ – ደስታ ጊቻሞ  – አበባው ቡታቆ

 ብርሀኑ በቀለ – አዲስዓለም ደበበ – ሙሉዓለም ረጋሳ

 
መስፍን ኪዳኔ  – በረከት ይስሃቅ – ብሩክ ኤልያስ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሰዒድ ሁሴን – ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

ሐብታሙ ተከስተ – ያስር ሙገርዋ – ሱራፌል ዳኛቸው

ሽመክት ጉግሳ – ኢዙ አዙካ  – አብዱርሀማን ሙባረክ