ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ

በአዳማው አበበ ቢቂላ ስታድየም አዳማን ከመቐለ የሚያገናኘው ሌላው የሳምንቱ ጨዋታ ቀጣዩ የቅድመ ዳሰሳ ትኩረታችን ነው። 

ከሚታወቅበት የወትሮው ተፎካካሪነቱ በተለየ ሁኔታ ከአራት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ይዞ 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አዳማ ከተማ አጀማመሩ እጅግ ደካማ ሆኗል። ዳዋ ሁቴሳ ሲዳማ ላይ ካስቆጠራት ግብ ውጪም ቡድኑ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ተስኖት ቆይቷል። በመሆኑም የነገው ጨዋታ በሜዳው እንደመደረጉ መጠን የመጀመሪያን ድል በማሳካት ነገሮችን ለማስተካከል የሚጥርበት እንደሚሆን ይታመናል። በአምስተኛው ሳምንት ያልተጫወቱት መቐለዎች በአንፃሩ በሁለት ተከታታይ ድሎች ከተጋጣሚያቸው በተለየ ሁኔታ ነበር ሊጉን የጀመሩት። ሆኖም በሦስተኛው ሳምንት ሶዶ ላይ ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ ነው ወደ አዳማ የሚያቀኑት። አምና ከዋንጫ ተፎካካሪዎቹ መከከል የነበሩት መቐለዎች ዘንድሮም በተመሳሳይ መንገድ ለመቀጠል ከድቻው ሽንፈት በፍጥነት አገግመው ወደ ድል መመለስ ይጠበቅባቸዋል።  

አዳማ ከተማዎች ጉዳት ላይ የሚገኙት ቁልፍ ተጫዋቾቻቸው ከነዓን ማርክነህ እና ቡልቻ ሹራ አገግመው ለጨዋታው የመድረሳቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። ሌላኛው የቡድኑ አማካይ ዐመለ ሚልኪያስ ግን በጉዳት ሙሉ ለሙሉ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል። መቐለ 70 እንደርታዎች በአንፃሩ ያለ ጉዳት እና ቅጣት ዜና ሙሉ ስብስባቸውን ይዘው ነው ወደ አዳማ ያመሩት።

የአዳማ ከተማ የማጥቃት ኃላፊነት በዳዋ ሁቴሳ እና በረከት ደስታ ላይ የተጣለ ይመስላል። በሁለቱ መስመሮች የሚሰለፉት ተጫዋቾች ከሚደርሷቸው ኳሶች በመቐለ የመሀል እና የመስመር ተከላካዮች መሀል ለመግባት የሚያደርጉት ጥረትም ይጠበቃል። ሆኖም በመቐለ ጠንካራ የኃላ ክፍል ክፍተቶችን ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት ጠንካራ ፈተና እንደሚገጥመው መናገር ከባድ አይሆንም። ጠንቀቅ ያለ አቀራረብ ሊኖራቸው የሚችሉት መቐለዎችም ቢሆኑ በነአማኑኤል ገብረሚካኤል እና ያሬድ ከበደ የሚፈጥሩት ጫና በግዙፎቹ የአዳማ ተከላካዮች መፈተኑ አይቀርም። በመሆኑም በጨዋታው ጎሎች በቀላሉ ይገኛሉ ብሎ መገመት የሚያስቸግር ሲሆን ምንአልባትም ቀድሞ ግብ የሚያስቆጥረው በድን የተሻለ ዕድል ሊኖረው እንደሚችል መናገር ይቻላል። 

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች 

– መቐለ ሊጉን በተቀላቀለበተ የ2010 የውድድር ዓመት ከተደረጉት ሁለት ጨዋታዎች ውስጥ የመጀመሪያው በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ በሁለተኛው መቐለ አሸናፊ ሆኗል፡

– በሁለቱ ጨዋታዎች መቐለ ሦስት አዳማ ደግሞ አንድ ግቦችን አስቆጥረዋል፡፡

– በሁለተኛው ዙር አዳማ ላይ መቐለ 2-0 ያሸነፈበት ውጤት የአዳማን በሜዳው ያደረገውን የሠላሳ ጨዋታዎች የለመሸነፍ ጉዞ ያስቆመ ነበር፡፡

ዳኛ 

– በመጀመሪያው ሳምንት አንድ ቢጫ ካርድ ብቻ የመዘዘበትን የመቐለ እና ደደቢት ጨዋታ የመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው በዚህ ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ተመድቧል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ሮበርት ኦዶንካራ

አንዳርጋቸው ይላቅ – ምኞት ደበበ – ተስፋዬ በቀለ – ቴዎድሮስ በቀለ

አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ – ሱሌይማን ሰሚድ

ዳዋ ሆቴሳ – ሙሉቀን ታሪኩ – በረከት ደስታ

መቐለ 70 እንደርታ

ፍሊፕ ኦቮኖ

ሥዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – አሚን ነስሩ – ያሬድ ሀሰን

ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ

አማኑኤል ገ/ሚካኤል – ኃይደር ሸረፋ – ሳሙኤል ሳሊሶ

ያሬድ ከበደ