የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 3-1 መቐለ 70 እንደርታ

አዳማ ከተማ በሜዳው መቐለ 70 እንደርታን አስተናግዶ የመጀመሪያ የሊግ ድሉን ባሳካበት የዛሬው የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተካታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።

” ማሸነፍ ይገባናል ፤ በተሻለ መልኩ ወደ ጎል እንደመድረሳችን ከዚህም በላይ ማስቆጠር ነበረብን።” ሲሳይ አብርሀም – አዳማ ከተማ

ስለጨዋታው…

” ጨዋታው ጥሩ ነበር። በሜዳችን የግድ ሦስት ነጥብ መያዝ አለብን ብለን ነው የተጫወትነው። ጥሩ ነበርን ፤ ማሸነፍ ይገባናል በተሻለ መልኩ ወደ ጎል እንደመድረሳችን ከዚህም በላይ ማስቆጠር ነበረብን። ተጫዋቾቼ ጨዋታውን እንድናሸንፍ ለከፈሉት መስዋትነትም ማመስገን እፈልጋለው። ካለንበት ደረጃ ለመውጣት ውጤቱ ያስፈልገን ስለነበርም በማሸነፋችን በጣም ደስ ብሎኛል። ”

ከእስካሁኖቹ ጨዋታዎች አንፃር ዛሬ ቡድኑ ላይ የታየ የተለየ ነገር…

” ዛሬ ተጫዋቾቼ የተሻለ መነሳሳት እና ፅናት ነበራቸው። እርስ በርስም ተነጋርግረው ነበር የገቡት። ተሰብስበው ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ ኃላፊነት እንደሚወስዱ ተነጋግረው ነበር። ያሰቡትን በማሳካታቸው በጣም ደስ ብሎኛል። ”

ስለ ከንዓን ማርክነህ የዕለቱ ብቃት…

” ምንም ጥያቄ የለውም ከንዓን ድንቅ አማካይ ነው። ሀገርቷ ውስጥ ካሉት አማካዮች በማጥቃት ባህሪው አለ የምትለው ተጫዋች ነው። ዛሬም እንደቡድን ሁሉም ጥሩ ነበሩ ፤ ከንዓንም የጨዋታው ኮከብ ነበር። ”


” እንደቡድን ስናየው ዛሬ ጥሩ አልነበርንም” ገብረመድህን ኃይሌ – መቐለ 70 እንደርታ

ስለጨዋታው…

” ጨዋታው እንደተመለከትነው በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ከተቆጠሩብን ጎሎች ሁለተኛው ጎል በመልሶ ማጥቃት የመጣ ነበር። እዛ ላይ ስህተት ሰርተናል። መጠበቅ አልቻልንም። ያም ብዙ ነገር አበላሽቶብናል። ጨዋታው በአጠቃላይ በመጀመሪያው አጋማሽ ውጥረት የነበረበት ነበር። በጉልበት በልጠውን ነበር። ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀማቸውም አሸንፈውናል። እንደቡድን ስናየው ቡድናችን ዛሬ ጥሩ አልነበረም። በቀጣይ ስህተቶቻችንን አርመን ለመቅረብ እንጥራለን።”

የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ችግር…

” የተጋጣሚን ተጫዋቾች በመቆጣጠር ላይ ትኩረት በማድረጋችን ብዙ አቅም አውጥተናል። በመሆኑም በማጥቃት ሂደት ላይ ጥሩ አልነበርንም። ከወገብ በታችም ባለው የመከላከል እንቅስቃሴያችንም ደካማ ነበርን። በመሆኑም ልንሸነፍ ችለናል። ”

ያልተለመደው የአማኑኤል እና የሚካኤል ቅያሪዎች…

” የሚካኤል ቅያሪ ለማጥቃት ከመፈለግ የመነጨ ነው። የተሻለ ማጥቃቱን የሚያግዝ ተጫዋች በማስፈለጉ የተደረገ ቅያሪ ነበር። አማኑኤል ያገኛቸውን ኳሶች በመቆጣጠርም ሆነ በአጠቃላይ የጨዋታ መንፈሱ ጥሩ አልነበረም። “