የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 1-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በኢትዮጵያ ዋንጫ የአምናው አሸናፊ መከላከያ ቅዱስ ጊዮርጊስን ገጥሞ በ52ኛው ደቂቃ ቴዎድሮስ ታፈሰ ባስቆጠራት ብቸኛ የቅጣት ምት ግብ 1ለ0 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜ ተሸጋግሯል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 “በሁለተኛው አጋማሽ የነበሩብንን ክፍተቶች አርመን የምንፈልገውን ውጤት አስጠብቀን መውጣት ችለናል፡፡”- ሥዩም ከበደ (መከላከያ)

ስለጨዋታው

“የዛሬው ጨዋታ በተለይ ለኛ ትልቅ ቦታ የሰጠነው ነበር። ባለፍነው ሳምንት ባደረገው የመጨረሻ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ሁለት ተጫዋቾች በቀይ ወጥተውብን 5ለ1 በሆነ ውጤት ተሸንፈናል። ከዛ ሽንፈት ለመውጣት በተለይ የዛሬው ውጤት በእጅጉ ያስፈልገን ነበር፡፡ በዛሬው ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ጊዮርጊሶች የተሻለ ተጭነው መጫወት ችለዋል። ሆኖም በሁለተኛው አጋማሽ የነበሩብንን ክፍተቶች አርመን የምንፈልገውን ውጤት አስጠብቀን መውጣት ችለናል፡፡”

“ብዙ እድሎችን ብንፈጥርም መጠቀም አልቻልንም”- ስቴዋርት ሃል (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው ውስጥ የነበረው አንድ ቡድን ብቻ ነበር፤ በጨዋታው 10 የሚሆኑ እድሎችን አምክነናል። በአንጻሩ በተጫዋቾች የተሰራው የመከላከል አጥር የተሻለ ነገር ማድረግ ይችላል ብለን ባሰብንበት አጋጣሚ ከቅጣት ምት ግብ አስተናግደናል፡፡ ተጫዋቾቻችን ኳሱ ሲመታ መዝለል እየቻሉ ነገር ግን አልዘለሉም፡፡ በመከላከሉ አንድ ስህተት ሰርተናል። በማጥቃቱ ረገድ 10 አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለናል፡፡የተሸነፍነው ብዙ እድሎችን ብንፈጥርም በጣም ከቅርብ ርቀት ሁሉ ግቦችን በማምከናችን ነበር። በአንጻሩ እነሱ ያገኙትን እድል በመጠቀማቸው ነው ያሸነፉት፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ስድስት ንፁህ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረናል፤ እነሱ ደግሞ አንድ አጋጣሚ ብቻ ነበር የፈጠሩት። በእረፍት ሰዓት ከተጫዋቾቼ ጋር የተነጋገርነው በሁለተኛው አጋማሽ የምናገኛቸውን አጋጣሚዎች ከመጀመሪያው በተሻለ መጠቀም እንዳለብን ነበር፤ ነገርግን ያንን ማድረግ አልቻልንም፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *