ሴቶች 1ኛ ዲቪዝዮን | አአ ከተማ እና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ነጥብ ተጋርተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን 13ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረገ አንድ ጨዋታ ሲጀመር አዲስ አበባ ከተማ እና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ነጥብ ተጋርተዋል።

በአዲስ አበባ ስታድየም 10:00 ላይ የተጀመረው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ታይቶበት 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በ2ኛው ደቂቃ ትደግ ፍስሀ ሳትጠቀምበት በቀረችው የግብ እድል እንዲሁም በ11ኛው ደቂቃ ቤዛዊት ተስፋዬ ባደረገችው ሙከራ ባለሜዳዎቹ ጎል የማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም አከታትለው ባስቆጠረነው ጎሎች መሪ መሆን የቻሉት እንግዶቹ ነበሩ። በ9ኛው ደቂቃ መቅደስ ማስረሻ ያሻገረችውን ኳስ ኝቦኝ የን በአግባቡ በመቆጣጠር ከጨዋታ ውጪ ናት በሚል ተዘናግተው የነበሩት ተከላካዮችን አምልጣ በመውጣት አክርራ መትታ አስቆጥራለች። አዲስ አበባዎች የአቻነት ግብ ለማግኘት ወደፊት ተስበው በሚጫወቱበት ሁኔታ በመልሶ ማጥቃት በ21ኛው ደቂቃ ጤናዬ ለታሞ ከቀኝ መስመር ያሳለፍችላትን ቅድስት በላቸው የግል ብቃቷን ተጠቅማ የግብ ጠባቂዋን አቋቋም ተመልክታ የመታችው ኳስ ከመረብ አርፎ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ 2-0 እንዲመራ አስችላለች።

ከግቡ መቆጠር ከሁለት ደቂቃ በኋላ ቤዛዊት ተስፋዬ ከህይወት ረጋ የተቀበለችውን ኳስ ወደ ግብነት ለውጣ ልዩነቱን በማጥበብ አአ ከተማን ወደ ጨዋታው የመለሰች ሲሆን በቀሪ የመጀመርያ አጋማሽ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ተደርጎበት ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት እረፍት ወጥተዋል።

ከዕረፍት መልስ አዲስ አበባዎች ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን በተለይም ተቀይራ የገባችው ፎዚያ መሐመድ ስታደርገው የነበረው እንቅስቃሴ ለእንግዳው ቡድን የተከላካይ ክፍል የራስ ምታት ነበር። 64ኛው ደቂቃ ላይም ቤዛዊት ተስፋዬ ላይ በተሰራው ጥፋት የተሰጠውን ቅጣት ምት በቀጥታ በመምታት ወደግብነት ለውጣ ቡድኗን አቻ ማድረግ ችላለች።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ጥሩነሽ አካዳሚዎች በጤናዬ ለታሞ ያደረጉት ግብ ሙከራ ውጭ ተጨማሪ የግብ እድል መፍጠር ያልቻሉ ሲሆን በአዲስ አባባዎች በኩል ደግሞ በ70ኛው ደቂቃ ትደግ ፍስሀ ወደግብ አክራራ መታ ግብ ጠባቂዋ ያወጣችባት እንዲሁም ተቀይራ የገባችው ፍቅርተ ብርሃኑ የፈጠረችው እድል ይጠቀሳሉ።

በጨዋታው በ74ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስ አበባዋ ሰላም ለዓከ እና የጥሩነሽ አካዳሚዋ ጤናዬ ለታሞ እርስ በእርስ በመጋጨታቸው ጉዳት አስተናግደው ከሜዳ ወጥተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *