ቁጥራዊ መረጃዎች በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር የተቆጠሩ ግቦች ዙሪያ – ክፍል ሁለት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ ሊጀመር ተቃርቧል። በመጀመሪያው ዙር ከተመዘገቡ ግቦች በመነሳት የተለያዩ ቁጥራዊ መረጃዎችን በክፍል አንድ ፅሁፋችን ያስነበብን ሲሆን አሁን ደግሞ ግቦቹ የተቆጠሩባቸውን መንገዶች እና የጎል ምንጮች እንመለከታለን።

በሊጉ የመጀመሪያ ዙር በተደረጉ 120 ጨዋታዎች በጥቅሉ 227 ግቦች በአማካይ ደግሞ በጨዋታ 1.89 ግቦች ተቆጥረዋል። የእነዚህ ግቦች መነሻ መንገዶቻቸው ምን ምን ነበሩ የሚለውን በሁለት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን። በዚህም መሰረት 169 (74 በመቶ) የሚሆኑት ከክፍት ጨዋታ በተነሱ እንቅስቃሴዎች በተፈጠሩ የግብ ዕድሎች ከመረብ ያረፉ ነበሩ። በሌላ በኩል ቀሪዎቹ 58 ግቦች ደግሞ ከቆሙ ኳሶች የተገኙ ናቸው።

በቆሙ ኳሶች መነሻነት ወደ ግብነት ከተቀየሩት ኳሶች መካከል 31 የሚሆኑት በፍፁም ቅጣት ምቶች ናቸው። በውድድሩ እስካሁን ወደ ግብነት ያልተቀየሩት የፍፁም ቅጣት ምቶች ቁጥርም ሦስት ብቻ ነው። ከፍፁም ቅጣት ምት ውጪ በማዕዘን ምት እንዲሁም የቅጣት ምቶች መነሻነት በድምሩ 23 ግቦች የተመዘገቡ ሲሆን ይህም ከአጠቃላዩ የግብ መጠን አንፃር ሲታይ 11 በመቶ ብቻ የሚሆነውን ይዟል።


ንፃሬው በኢንተርናሽናል ውድድሮች ላይ የሚታይብን የቆሙ ኳሶች አጠቃቀም ችግር በሊጉ ላይም የሚንፀባረቅ ስለመሆኑ ማሳያ ቢሆንም በሌላኛው ጎኑ ልናየውም የምንችለው ነው። በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ እነዚሁ ኳሶችን የምንከላከልበት መንገድ ደካማነት ሲታይ ቢስተዋልም በሊጉ ላይ ግን የቡድኖቻችን የማጥቃት መንገዶች ለቆሙ ኳሶች የሚሰጡት አናሳ ትኩረት ደካማውን የመከላከል ሂደት ማለፍ የሚችልበት ደረጃ ላይ እንኳን እንደማይገኝም ያስገነዝበናል።

የተቆጠሩትን ግቦች በጨዋታ እንቅስቃሴ ከተጨዋቾች አስተዋፅዖ አኳያ መመልከትም ይቻላል። ከግቦቹ ውስጥ 166ቱ (73 በመቶ) የሚሆኑት የተጫዋቾች የማመቻቸት ሚና (Assist) የታዩባቸው ሆነዋል። ቀሪዎቹ 61 ግቦች (27 በመቶ) ደግሞ ምንጫቸውን በአራት ተከፍለው ተቀምጠዋል። ከነዚህ ውስጥ 31 የፍፁም ቅጣት ምቶች እንዳሉ ሆነው አራት ግቦች ደግሞ በራስ ላይ የተቆጠሩ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ሳላዲን ሰዒድ በሁለት እንዲሁም ባዬ ገዛኸኝ በአንድ አጋጣሚዎች ከቅጣት ምቶች በቀጥታ በመምታት ሲያስቆጥሩ ሚካኤል ደስታ ከማዕዘን ምት በቀጥታ በመምታት ያስመዘገበው ጎልም በዚሁ ውስጥ የሚካተት ነው።


ይህን ቁጥር ስንመለከተው በየጨዋታዎቹ ላይ በተደጋጋሚ የምንሰማው የአርቢትሮችን ፊሽካን ተከትለው በተጋጣሚ የግብ ክልል ዙሪያ የሚገኙ የቅጣት ምት ዕድሎች በቀጥታ ተመተው ወደግብነት የሚቀየሩበት ንፃሬ እጅግ የወረደ መሆኑን እንገነዘባለን። እንዲሁም ቁጥሩ በየክለቡ የሚገኙ እና በቋሚነት የቅጣት ምቶችን የሚመቱ ተጫዋቾች ስኬታማነት በልልምምድ ወቅቶች ላይ ይበልጥ ሊፈተሹ እንደሚገባም ያመለክታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *