አሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 2-0 ስሑል ሽረ

ጅማ አባጅፋር ስሑል ሽረን 2-0 ካሸነፈ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡


“ከዚህ በኃላ በወጥ አቋም እንቀጥላለን” ዩሱፍ ዓሊ – ጅማ አባጅፋር

ከሜዳ ላይ ጨዋታዎች ውጭ የደምወዝና ተያያዥ ጥያቄዎች ወጥ የሆነ አቋም እንዳናሳይ ተፅዕኖ አሳድሮብናል። ከኦኪኪ ውጭ ሌሎች የውጭ ተጫዋቾች በደሞዝ ጥያቄ ምክንያት ልምምድ ሳይሰሩ ነበር ወደ ድሬዳዋ አቅንተን የተጫወትነው። እነዚህ ጥያቄዎች ውጤት ላይ ተፅዕኖ አሳድረዋል። ከድሬዳዋው መልስ ጥያቄአቸው ተቀርፏል። ከዚህ በኋላም እንደሚስተካከል ተነግሮናል። ከዚህ በኃላ በወጥ አቋም እንቀጥላለን፡፡

በኦኪኪ አፎላቢና በማማዱ ሲድቤ መካከል ስለተፈጠረው ግጭት

ሰዎች እንደመሆናቸው የራሳቸው ስሜት ይኖራቸዋል፤ ኦኪኪ ከመጣ በኋላ በደጋፊውም በክለቡም ለኦኪኪ የተሰጠው ትኩረት አሰከፍቶታል። ምክንያቱም የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አግቢ ነው። በሀገሪቱ ካሉ የውጭ ተጫዋቾችም በላይ ብዙ ግብ አለው። ለሱ የተሰጠው ትኩረት በማነሱ ስሜቱ ተነክቶ ነበር። ነገር ግን በመሀላቸው ያለውን ነገር ፈትተን ልምምድም በአንድ ላይ በጥሩ መንፈስ ሰርተን የዛሬውን ጨዋታ አከናውነናል፡፡

ያለተፈጥሯዊ የተከላካይ አማካይ ስለመቅረባቸው

ለዛሬው ጨዋታ በ4-2-2 ዳይመንድ የተጫወትነው ወደ ፊት በምንሄድበት ጊዜ በዛ ብለን የተጋጣሚ ግብ ክልል ውስጥ እንገኝ ነበር። በዚህም ተደጋጋሚ እድሎችን ስንፈጥር ነበር። በመከላከሉ ረገድ አስቻለውና ዲዲዬ ለብሬ ወደ መሀል እየገቡ እንዲሸፍኑ ነበር ያሰብነው። በዚህም ውጤታማ ነበርን፡፡

“በመጀመሪያው አጋማሽ በተከላካዮች ስህተት ግብ በማስተናገዳችን ያሰብነውን ነጥብ ማሳከት አልቻልንም’ ሳምሶን አየለ – ስሑል ሽረ

ላለመውረድ እንዲሁም ከሜዳ ውጭ እንደመጫወታችን ተፅእኖ ነበረብን። በዚህም ላይ ጠንካራ የመከላከል አቅም የነበራቸው እንደ ዲሜጥሮስ ያሉ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ካለመሰለፋቸው በተጨማሪ በመጀመሪያው አጋማሽ በተከላካዮች ስህተት ግብ በማስተናገዳችን ያሰብነውን ነጥብ ማሳከት አልቻልንም።

ስለ ቀጣይ

በሁለተኛው ዙር ቡድኑ እንደ አዲስ ፈርሶ እንደመሰራቱ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ መሻሻሎች አሉ። በሜዳችንና ከሜዳችን ውጭ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች ወጥ የሆነ አቋም ለማሳየት እና ውጤታችንን ለማሻሻል ጥረት እናደርጋለን፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡