የአሰልጣኞች አስተያየት | ደደቢት 2-3 ድሬዳዋ ከተማ

በ20ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከተካሄዱት ጨዋታዎች መካከል መቐለ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ደደቢትን 3-2 ከረታበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሚከተለውን ብለዋል።

“ቡድናችን በጥሩ ደረጃ እንዲጨርስ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እንደሚጠብቀን እናውቃለን፤ ያንን ደግሞ አሁን ጀምረነዋል” ስምዖን ዓባይ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ሁለት መልክ ነበረው። ከዕረፍት በፊት በነበረው እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ብልጫ ወስደን አሸንፈን ነው የወጣነው። ከዕረፍት በኃላ ግን ደደቢቶች ተጭነው ተጫውተዋል። ያ ስለሆነም ነው ሁለት ጎል ጰዘማስቆጠር የቻሉት። መጀመርያ አጋማሽ የነበረው እንቅስቃሴ ማስቀጠል ብንችል ኖሮ የተሻለ ጎሎች ማግባት እንችል ነበር።
መጀመርያ አጋማሽ፤ ሁለተኛው አጋማሽ ደሞ እነሱ ጥሩ ነበሩ። ውጤቱ በዚህ መጠናቀቁም ለኛ ጥሩ ነገር አለው። ምክንያቱም ካለንበት ሁኔታ አንፃር ተከታታይ ጨዋታ ማሸነፍ በዚ ሰዓት ጥሩ ነው።

ድሬዳዋን በሊጉ ለማቆየት ምን የተለየ ነገር እንጠብቅ? 

በቀጣይ ጨዋታዎች ላለመውረድ የሚደረጉ ፉክክሮች ከፍተኛ ናቸው። ከባድ ጨዋታዎች ናቸው ከሜዳችን ውጭ ያሉት። በጨዋታዎቹ በተቻለ መጠን ጥሩ ውጤት በማምጣት ቡድናችን በጥሩ ደረጃ እንዲጨርስ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እንደሚጠብቀን እናውቃለን። ያንን ደሞ አሁን ጀምረነዋል። አጠናክረን ለመሄድ ደሞ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን።

” ከሜዳ ውጭ አሸንፈን በመምጣታችን ተጫዋቾቼ ከልክ ያለፈ ጉጉት ነበራቸው” ዳንኤል ፀሃዬ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው እኛ በምንፈልገው መንገድ አልሄደም።
ተጫዋቾቼ ከሜዳ ውጭ አሸንፈን በመምጣታችን ከልክ ያለፈ ጉጉት ነበራቸው። በርግጥ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ አላደረግንም። አንዳንድ ተጫዋቾች በተናጠል ካደረጉት ውጭ እንደ ቡድን ጥሩ አልነበርንም። ሽንፈቱም እንቀበለዋለን።

ውጤቱ ጨዋታውን ይገልፀዋል?

ከዕረፍት በፊት እነሱ የተሻሉ ነበሩ። ከዕረፍት በኃላ ደግሞ ወደ ፊት በመሄድ ጥሩ ሙከራዎች አድርገን ነበር። ጎልም አግብተን ነበር። የተቆረጠ ኳስ ከጨዋታ ውጭ የሚባል የለም። መድሃኔ ያገባው ግብ የተቆረጠ ኳስ ነበር። ዳኛው ግን ትልቅ ችግር ነበር። ባለፈው ሳምንት ከቡና በነበረው ጨዋታም እንደዚህ፤ እዚ መጥተንም ያው። የዳኛ ተፅዕኖ ትልቅ ነው። ግን ይህ እኛን ስለማይመለከት የሚመለከተው አካል ማየት በሚችለው ነው የሚያየው። የነሱ ተፅዕኖ እኛ ውጤታማ እንዳንሆን አድርጎናል።

መስራት የሚገባንን ሰርተን በፕሪምየር ሊጉ ለመቆየት ገና ነው አስር ጨዋታዎች ይቀሩናል። አስር ነጥብ ማለት ሰላሳ ነጥብ ነው። ከሜዳችን ውጪ አሸንፈን መምጣታችን ወዳልሆነ ስሜት ውስጥ ከቶናል። በቀጣይ ግን በስነ ልቦና መስራት የሚገባንን ሰርተን እስከመጨረሻው እንታገላለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡