ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ሀዋሳ ከተማን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሦስተኛ ከፍ አድርጓል

ሁለቱ የሀዋሳ ክለቦችን ያገናኘው የሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና የ23ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በስሑል ሽረ ሰፊ ሽንፈት የገጠመው ሀዋሳ ከተጠቀመበት ስብስብ ውስጥ በሦስት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን አድርጎ ተክለማርያም ሻንቆ፣ አዲስዓለም ተስፋዬ እና ምንተስኖት አበራን በማሳረፍ ሶሆሆ ሜንሳህ፣ ዳንኤል ደርቤ እና ሄኖክ ድልቢን ሲጠቀም በጅማ አባጅፋር ሽንፈት ገጥሞት የተመለሰው ሲዳማ ቡና በአንፃሩ ተስፉ ኤልያስን በሚሊዮን ሰለሞን ብቻ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

በቅርቡ ህይወቱ ላለፈው የዋልታ ፖሊስ ተጫዋች አማኑኤል ብርሀነ የህሊና ፀሎት ከተደረገ በኋላ   በኃይለየሱስ ባዘዘው የመሐል ዳኝነት የተጀመረው ጨዋታ እንደተጠበቀው ያልነበረ እንቅስቃሴን አሳይቶን አልፏል። ሀዋሳዎች የአማካዩ ታፈሰ ሰለሞን ያለመኖር ታክሎበት በመሀል ሜዳ ላይ የነበራቸውን ብልጫ ለማሳየት ሲቸገሩ ሲሆን ሲዳማ ቡናዎችም የፈጣሪ አማካዩ ዳዊት መቀዛቀዝን ተከትሎ ከግርማ በቀለ እና ዮሴፍ እግር ስር በረጅሙ ወደ ቀኝ መስመር ለሐብታሙ ገዛኸኝ በሚጣሉ ኳሶች ቀጥተኛ ጥቃትን ምርጫቸው አድርገው ተጫውተዋል፡፡

ገና በጨዋታው ጅማሮ ከመሐል ሜዳ የዳኛው ፊሽካ እንደተሰማ በቀኝ በኩል ሐብታሙ ገዛኸኝ እየነዳ ወደ ሳጥን ጠርዝ ተጠግቶ መትቶ በተከላካዮች ስትመለስ በድጋሚ አዲስ ግደይ መትቶ ከግቡ መስመር ላይ መሳይ ጳውሎስ በግሩም ሁኔታ ያወጣው ኳስ ሲዳማ ቡናን ከና በጊዜ ለግብ ያቃረበች አጋጣሚ ነበረች። በሀዋሳዎች በኩል ደግሞ 8ኛው ደቂቃ ፍቅረየሱስ እና ደስታ በአንድ ሁለት ተቀባብለው በረጅሙ ለዳንኤል አሻግረውለት ዳንኤል በቀጥታ ወደ ግብ መቶ የግቡ ቋሚ ታካ የወጣችበት የመጀመርያ ሙከራቸው ነበረች።

የሀዋሳ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ የቅብብል ስህተቶች ሲሰሩ የታየ ሲሆን በመከላከሉ ረገድም ተጋላጭ ነበሩ። በተለይ የመሳይ ጳውሎስ ገና በጊዜ ተጎድቶ መውጣት የመከላከል ክፍል ክፍተቱን አጉልቶታል። በዚህም ቡናዎች በቀኝ መስመር በኩል ወደ ማጥቃት ወረዳው በመድረስ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። 13ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ የቅብብል ስህተት የተገኘችን ኳስ ግሩም አሰፋ ለሐብታሙ ሰቶት ሐብታሙ ሰብሮ በመግባት ወደ ግብ መትቶ ብረቱ ሲመልስ ይገዙ ቦጋለ ጋር ደርሳ አጥቂው ሲመታት ሶሆሆ ሜንሳህ እንደምንም አውጥቶበታል፡፡ በ29ኛው ደቂቃ ሲዳማዎች ነቅለው ለማጥቃት ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ሲሄዱ በተነጠቀ ኳስ ደስታ በግራ አቅጣጫ ወደ ውስጥ የጣለውን ኳስ ፍቅሩ ወዴሳ ተዘናግቶ ፍቅረየሱስ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ ቢያገኝም መጠቀም አልቻለም፡፡

33ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ሐብታሙ እና ዳዊት ተቀባብለው ከዳዊት እግር ስር ተከላካዩ ላውረንስ ሲነጥቀው ከጀርባው የነበረው አዲስ ግደይ አግኝቶ ከሳጥን ውጪ ከርቀት አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥሮ ሲዳማን መሪ አድርጓል፡፡ 45ኛው ደቂቃ ሀዋሳዎች አቻ ሊሆኑ የሚችሉበትን አጋጣሚን አግኝተው ነበር፤ ዳንኤል ደርቤ ወደ ሳጥን የላካትን ኳስ እስራኤል ክፍት እድል አግኝቶ ብረቱ መልሶበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ ተሻሽሎ ሲቀርብ ቀዝቀዝ ብለው ጉልበት ላይ ትኩረት በማድረግ አጋማሹን የጀመሩት ሲዳማዎች ከመልሶ ማጥቃት በሚገኙ እድሎች ማጥቃትን ምርጫቸው አድርገዋል። አዳነ ግርማን እና ሄኖክ ድልቢን ቀይረው በተከታታይ ሁለቱን ወጣቶች መስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነን ወደ ሜዳ ያስገቡት ሀይቆቹ ብልጫን መውሰድ ሲችሉ በመጀመርያዎቹ አምስት ደቂቃዎችም ከሁለቱም በኩል ሙከራዎች ታይተዋል። 47ኛው ደቂቃ ኬኒያዊው ተከላካይ ሰንደይ ሙቱኩ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ እስራኤል ከእግሩ ነጥቆ በቀጥታ የመታት ኳስ በግቡ ቋሚ ያለፈችው የሁለተኛው አጋማሽ ቀዳሚዋ መከራ ነበረች፡፡ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ከቀኝ መስመር ሐብታሙ ያሻገረውን አዲስ መትቶ ሶሆሆ ሲያወጣበት አማካዩ ዳዊት ተፈራ ከርቀት መትቶ እንደምንም ያወጣበትም ተጠቃሽ ነበር፡፡

የመጨረሻዎቹን 20 ደቂቃዎች ብልጫቸውን አጠናክረው ሲያሳዩ የነበሩት ሀዋሳዎች በርካታ የማጥቃት አጋጣሚን መፍጠር ቢችሉም የሲዳማን የተከላካይ መስመር መስበር አልቻሉም፡፡ 60ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሐንስ በግምት 40 ሜትር ላይ አክርሮ የመታትን ኳስ ፍቅሩ ወዴሳ በግሩም ብቃት ወደ ውጪ አውጥቶበታል፡፡ 85ኛው ደቂቃ ብሩክ ያመቻቸለትን መስፍን ታፈሰ መትቶ የግቡ ብረት ሲመልስበት ከዚህ በተጨማሪ በእስራኤል እሸቱ ሁለት ጊዜን በጭማሪ ሰዓት ማግኘት ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በድሉ በመታገዝ ሲዳማ ቡና ነጥቡን 40 በማድረስ ወደ ሶስተኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በ30 ነጥብ 10ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: