ሪፖርት | አዳማ ከተማ እና መከላከያ ያለግብ ተለያይተዋል

በ24ኛው ሳምንት የሊጉ መረሐ ግብር አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ አዳማ ከተማ መከላከያን ያስተናገደበት ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።

አዳማ ከተማ በደቡብ ፖሊስ 2-0 ከተሸነፈው ስብስብ ውስጥ ሱለይማን መሐመድ እና ሙሉቀን ታሪኩን በማሳረፍ ተስፍዬ በቀለ እና ከነዓን ማርክነህን የተካ ሲሆን በእንግዳው ቡድን መከላከያ በኩል ደግሞ ባህር ዳርን 1-0 ካሸነፈው ቡድን አበበ ጥላሁን በአዲሱ ተስፋዬ ተተክቷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የቀዘቀዘ የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን በሙከራ ደረጃ አዳማ ከተማዎች የተሻሉ ነበሩ። በዚህም በ8ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ ከአዲስ ህንፃ የተሻገረለትን ኳስ ሱሌይማን ሰሚድ ወደ ግብ አክርሮ ሞክሮ በግብ ጠባቂው ተመልሶበታል። የባለሜዳዎቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ግራ መስመር አዘንብሎ በረከት ደስታ እና ቡልቻ ሹራ ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር። ከመሀል ከአዲስ ህንፃ እና ከነዓን ማርክነህ ወደ ግራ መስመር የሚጣሉ ኳሶችም የመከላከያን የቀኝ የመከላከል ወገን መፈተናቸው አልቀረም። 10ኛው ደቂቃ ላይ ቡልቻ ሹራ ከከነዓን የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ አክርሮ ሲመታ ወደ ግራው ቋሚ ተጠግቶ የወጣበት ሙከራም በዚህ ረገድ የሚነሳ ነው። ከዚህ ውጪ አዳማ ከተማዎች የመከላከያን ተከላካዮች ሰብረው መግባት በመቸገራቸው ከርቀት የሚመቷቸው ኳሶች በተከላካዮች ሲደረቡም ይታይ ነበር።

በመከላከያ በኩል 20ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ታዬ ከቀኝ መስመር የሳጥን ጠረዝ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂ ያዳነበት በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የሚባል ሙከራ ነበር። መሀል ላይ በዳዊት እስጢፋኖስ እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት አድርገው የሚጫወቱት መከላከያዎች ከዳዊት ወደ ፍሬው ሰለሞን ከሚሻገሩ የመልሶ ማጥቃት ኳሶች መነሻነት የተሻለ የሚባል አጋጣሚ ሲፈጥሩ ይታይ ነበር። 37ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ከቀኝ ሳጥን ጠርዝ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ ሌላ የሚጠቀስ የቡድኑ መልካም አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

ሁለተኛ አጋማሽ የተሻለ ተጭነው መጫወት የቻሉት አዳማዎች የፊት መስመራቸውን ለማጠናከር በርካታ ለውጦችን በመጀመሪያው 15 ደቂቃ አድርገው ቢገቡም ግብ ማግኝት አልቻሉም ። በሙከራ ደረጃ 57ኛው ደቂቃ ላይ ከነዓን ማርክነህ ሳጥን ውስጥ ያገኝውን ኳስ በቀጥታ ወደግብ አክርሮ ሞክሮ አቤል ማሞ በቀላሉ አድኖበታል። አዳማዎች በተደጋጋሚ ከሳጥን ውጪ አክርረው የሚመቷቸው ኳሶችም ተከላካዮችን ማለፍ አልተቻላቸውም።

ባለሜዳዎቹ በመስመር በማጥቃት ይበልጥ ተጭነው የመጫወት ሂደታቸውን አጠናክረው በዱላ ሙላቱ እና ፉአድ ፈረጅ አማካኝነት በአዲስ ኃይል ቡልቻ ሹራን በማገዝ ከመስመር ኳሶችን ወደ ሳጥን በማሻማት ጫና ቢፈጥሩም አሁንም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። ሆኖም በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ በተደጋጋሚ ከቅጣት ምት የተገኙ የቆሙ ኳሶችን ቡልቻ ሹራ ወደ ግብ አክርሮ የሞከረባቸው አጋጣሚዎች ጥሩ የሚባሉ ነበሩ።

በእንግዳዎቹ በኩል መልሶ ማጥቃትን ምርጫ አድርገው ውጤት ለማስጠበቅ በጥንቃቄ በመከላከል ግቦችን ለማግኝት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በሙከራ ደረጃ 69ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በመልሶ ማጥቃት የተሻገረለትን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ጃኮ ፔንዜ ያመከነበት መልካም የሚባለው አጋጣሚ ነበር።

ጨዋታው ያለግብ ሲጠናቀቅ ውጤቱን ተከትሎ አዳማ በ30 ነጥብ 11ኛ መከላከያ ደግሞ በ25 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: