ሪፖርት | ፋሲል ከነማ የሊጉን አናት ተቆናጠጠ

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል በዐፄ ፋሲለደስ ስታዲየም የተደረገው የፋሲል ከነማ እና የጅማ አባጅፋር ጨዋታ በፋሲል ከነማ የበላይነት 6-1 ሲጠናቀቅ የሊጉን መሪነትም ከመቐለ 70 እንደርታ ተረከበ።

ከጨዋታው አስቀድሞ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ማኅበር በጅማ አባጅፋር በመጫወት ላይ የሚገኙት የቀድሞ የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች ከድር ኸይሪዲን እና ሄኖክ ገምቴሳን በማመስገን ስጦታ አበርክተውላቸዋል።

በደመናማ የአየር ፀባይ በጀመረው ጨዋታ ፋሲል ከነማዎች ባሳለፍነው ሳምንት ጎንደር ላይ ከወልዋሎ ጋር በነበረው ጨዋታ 1–0 ካሸነፈው ቡድን ምንም ዓይነት ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ በተቃራኒው እንግዳዎቹ ጅማ አባ ጅፋሮች በሜዳቸው ከሀዋሳ ጋር 1ለ1 ከተለያየው ቡድናቸው 5 ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። ዐወት ገ/ሚካኤል፣ ከድር ኸይረዲን፣ አክሊሉ ዋለልኝ፣ መስዑድ መሐመድ እና ኦኪኪ አፎላቢ በመተካት ተስፋዬ መላኩ፣ መላኩ ወልዴ ፣ ንጋቱ ገ/ሥላሴ፣ ብሩክ ገ/አብ እና ማማዱ ሲዲቤ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ፋሲል ከነማዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በማድረግ በጎሎች የታጀብ በበላይነት አሳይተው ወጥተዋል። በፈጣን የማጥቃት ሽግግር በ6ኛው ደቂቃ ኢዙ አዙካ ከመሐል ሜዳ ከኤፍሬም ዓለሙ የተቀበለውን ኳስ የግቡ ቋሚ የመለሰበት፤ ከሁለት ደቂቃ በኋላ በድጋሚ ከያሬድ ባየህ የተሻማውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ አገባው ሲባል የጅማ ተከላካዮች ከኋላ በመምጣት ጎል ከመሆን የታደገበት ሙከራዎች ዐፄዎች ብልጫ ወስደው ለመጫወታቸው ማሳያ ነበር። በዚሁ ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎቻቸው የቀጠሉት ፋሲሎች 19ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ከሳጥን ውጭ የተገኘውን ቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው በቀጥታ ወደ ጎል መትቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰው ጎል መሆን የሚችል እድል ነበር። ዐፄዎቹ ጎል የማግባት ጥረታቸው ተሳክቶ 25ኛው ደቂቃ በዛብህ መለዮ ከመሃል ሜዳ ነጥቆ ያመጣውን ኳስ አክርሮ ወደ ግብ ሲመታው ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ኳሱን መቆጣጠር ሳይችል የተፋውን ሙጂብ ቃሲም ወደ ጎል ቀይሮ ቀዳሚ መሆን ቻሉ።

ፋሲሎች ከጎሉ መቆጠር በኋላም ጫና ፈጥረው ፍጥነት የተሞላበት ጨዋታ ማሳየት የቻሉ ሲሆን በ32ኛው ደቂቃ ሳጥን ውስጥ የጅማ ተከላካዮች በዛብህ መለዮ ላይ በሰሩት ጥፋት ለፋሲል ከነማ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ኢዙ አዙካ ወደ ጎልነት ቀይሮታል። በቀሩት ደቂቃዎች ደቂቃዎች ላይ ፍጥነት የተሞላበት ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች የታየ ቢሆንም እንግድዶቹ አባጅፋሮች ኤልያስ አታሮ በግሉ ወደ ፊት በመሄድ አደጋ ለመፍጠር ከሚያደርገው ጥረት ውጭ የተሳካ ይግብ ለመፍጠር ተቸግረው እንደነበር ለማየት ተችሏል።

ልዩ ሆነው የዋሉት ፋሲሎች ከብዙ የመሐል ሜዳ ንኪኪ በኋላ ግራ መስመር ኢዙ አዙካ ኳሱን ይዞ በመግባት በጥሩ አቋቋም ለሚገኘው ሙጂብ ቃሲም ያሻማውን በአስደናቂ ሁኔታ በጭንቅላቱ ኳሱን ከመሬት ጋር አንጥሮ ለፋሲሎች ሦስተኛ ለራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

ከዕረፍት መልስ በተመሳሳይ የጨዋታ የበላይነት የጅማን የግብ ክልልን ሲፈትሹ የዋሉት ዐፄዎቹ 55ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ ከመሐል ነጥቆ ለሰዒድ ሐሰን በቀኝ መስመር ያቀበለውን ሰዒድ ሐሰን ወደ ጎል ቢሞክርም በጎሉ ጫፍ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል። ከአንድ ደቂቃ በኋላ ኢዙ አዙካ ከመሐል የተሻገረለትን ኳስ ተቀብሎ ሳይጠበቅ በቀኝ እግሩ አክርሮ ወደ ግብ በመምታት ለራሱ ሁለተኛ ለፋሲሎች አራተኛ ጎል አስቆጥሯል። ከዚህ በኋላ በተሻለ ብልጫ ወስደው መንቀሳቀስ የቻሉት ጅማዎች 64ኛው ደቂቃ በዲዲየ ለብሪ አማካኝነት ማስተዛዘኛ አንድ ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ዲዲየ ለብሪ ተደጋጋሚ ሙከዎችን ያደረገ ቢሆንም የፋሲሉ ግብጠባቂ ሳማኪ በጥሩ ብቃት ጎል እንዳይሆን አድርጎበታል።

በጨዋታው በቀኝ መስመር በኩል ጥሩ ውጤታማ የሆኑ ኳሶችን ሲያቀብል የነበረው የፋሲሉ የቀኝ መስመር ተከላካይ ሰዒድ ሐሰን 69ኛው ደቂቃ ላይ ለሙጂብ ቃሲም ጨርሶ ያቀበለውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በግሩም ሁኔታ አምስተኛ ጎል ለዐፄዎቹ አስቆጥሮ ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል። ሙጂብ ቃሲም ድንቅ ሆኖ በዋለበት በዚህ ጨዋታ በድጋሚ በ72ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ከሰዒድ ሐሰን የተሻገረለትን ኳስ ለራሱ አራተኛ ለክለቡ ስድስተኛ ጎል አስቆጥሯል። በመጨረሻም ጅማዎች ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል በ90+3ኛው ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ማማዱ ሲዲቤ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ጨዋታው በፋሲል ከነማ ፍፁም የበላይነት 6-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በዚህም ውጤት መሰረት ፋሲል ከነማ መሪው መቐለ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ የሊጉ መሪ የሆነበትን ውጤት አስመዝግቧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡