ዘካሪያስ ቱጂ ወደ ሜዳ መመለስን ያልማል


ለወራት ከሜዳ የራቀው ዘካሪያስ ቱጂ ስላለበት ሁኔታ እና በተሻለ አቅም ወደ ሜዳ ስለመመለስ ሀሳቡን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።

ከአስኮ የእግር ኳስ ፕሮጀክት እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን አሳልፎ በ2006 ወደ ፈረሰኞቹ ዋናው ቡድን ማደግ የቻለው ዘካርያስ ቱጂ ጥሩ አጀማመር በማድረግ ከመደበኛ ተሰላፊነት በተጨማሪ በአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ተካቶ ጨዋታዎች ማድረግ ችሎ ነበር። ሆኖም የቅዱስ ጊዮርጊስን የመጨረሻ ዓመት ቆይታ ብዙም የመጫወት እድል ማግኘት ያልቻለ ሲሆን አምና ወደ ኤሌክትሪክ አምርቶ የመጀመሪያውን ዓመት መጫወት ከቻለ በኋላ ዘንድሮ ሳንመለከተው ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ተጫዋቹ የት ነው ለሚለው ጥያቄ ሶከር ኢትዮጵያ በሚከተለው መልኩ ከተጫዋቹ ምላሽን አግኝታለች፡፡

“ከሜዳ የራቅኩት ከኤሌክትሪክ ጋር ባለመስማማት በተፈጠረ ግጭት ነው። አዲስ አሰልጣኝ ከመጣ በኋላ በአካልም አልተገናኘንም፤ ግን በስብሰባ ላይ አልተገኛችሁም በሚል ምክንያት ከክለቡ ጋር ተነጋግረን ተለያየን። ወቅቱ ደግሞ የዝውውር ጊዜው ያለቀበት ሰዓት ስለሆነ በዚህ ምክንያት ከሜዳ ልርቅ ችያለሁ። ይህን ያህል ጊዜ ጉዳት ሳይኖርብኝ ከሜዳ መራቄ ለኔ የራስ ምታት ፈጥሮብኝ ቆይቷል። እኔ የመጫወት እና ኤሌክትሪክን በደንብ ለማገልገል ፍላጎት ነበረኝ። ያ ግን አልሆነም። ኤሌክትሪክ ውል ስለነበረብኝ ባለፈው ክረምት ይፈርሳል፤ ይቀጥላል የሚሉ ግርታዎችም ስለነበሩ አዘናጉኝ። በኔ ቦታ ደግሞ አሰልጣኙ ሌላ ተጫዋች አመጣ። እነኚህ ሁሉ ምክንዬቶች ከዝውውር ጊዜም መዘጋት ጋር ተደማምረው ከሜዳ አጥፍተውኛል።

” አሁን ግን በውስጤ ያለው እልህ እና ቁጭት ነው። በተከታታይ ጨዋታ ላይ ተሰልፈህ ትጫወት የነበርክ ተጫዋች ያለ ስራ ስትቀመጥ እጅግ ከባድ ነው። እኔ ኳስ ገና አልጀመርኩም ማለት እችላለሁ። መጫወትን የማበቃበት ጊዜ አይደለም። ለተወሰነ ጊዜ አህምሮ ይረበሻል፤ ብዙ ነገርም ሊፈጠር ይችላል። እኔ ግን በግሌ እና ከሰፈር ልጆች ጋር (አስኮ ሜዳ) በመሆን እየሰራሁ ነው። እኔ ጤነኛ ነኝ የመጫወት አቅም በደንብ አለኝ። የሚቀጥለው ዓመት እንደምጫወት እርግጠኛ ነኝ። ይህ ዓመት ትምህርት የሰጠኝም ያሳጣኝም ዓመት ነው። 2012 ግን ሀሳቤን እንደማሳካ ለራሴ አሳምኜዋለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡