ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ደቡብ ፖሊስ

በዚህ ሳምንት ሀዋሳ ላይ በብቸኝነት የሚደረገውን ጨዋታ በዛሬው ዳሰሳችን በቅድሚያ እንመለከተዋለን።

በዋንጫ እና ላለመውረድ በሚደረጉት ፉክክሮች ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ሲዳማ እና ደቡብ ፖሊስ ለሁለቱም ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ያደርጋሉ። ውጤቱ እጅግ አስፈላጊያቸው በመሆኑም በቡድኖቹ ዘንድ ጥንቃቄ አዘል አቀራረብ እንደሚኖር ይጠበቃል። ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ለቻምፒዮንነት በሚደረገው ሩጫ ውስጥ ኮስታራ አቋም እንዳላቸው ያሳዩት ሲዳማዎች በሜዳቸው ካላቸው ጥንካሬ አንፃር ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ አሳክተው ወደ ላይ ከፍ ማለትን ያልማሉ። በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኙት ደቡብ ፖሊሶችም እምብዛም ወዳልራቋቸው ወላይታ ድቻ እና መከላከያ ለመድረስ የነገውን ከባድ ፈተና መወጣት የግድ ያላቸዋል።

ኢትዮጵያ ቡናን በረቱበት ጨዋታ አሁንም ከተከላካይ መስመር ጀርባ ክፍተት ካገኙ እጅግ አደገኛ መሆናቸው ያሳዩት ሲዳማ ቡናዎች በነገውም ጨዋታ መሰል ቅፅበቶችን መጠበቃቸው አይቀርም። ቀስ በቀስ በግራ እና በቀኝ መስመር ያለው የቡድኑ የማጥቃት ሚዛን እየተሻሻለ መምጣትም ከሁለቱ በአንደኛው አቅጣጫ ቡድኑ የሚከፍታቸው ጥቃቶች በፍጥነት ወደ መሀል እየጠበቡ ሲመጡ አልያም አቅጣጫ ሲቀይሩ ለተጋጣሚዎች ከባድ ይሆናሉ። መሀል ክፍል ላይም ከዳዊት ተፈራ የፈጠራ ብቃት በተጨማሪ በመጨረሻው ጨዋታ ሁለት ኳሶችን ለግብ ያመቻቸው ወንድሜነህ ዓይናለም ጥሩ አቋም ላይ መገኘት ለአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ቡድን ድንገተኛ ጥቃቶችን ከመሀል ለማስጀመር ጥሩ አማራጭን ይፈጥራል። ሆኖም የደቡብ ፖሊስ የተከላካይ ክፍል ከግብ ክልሉ አብዝቶ በመራቅ ላይንቀሳቀስ ስለሚችል ክፍተቶች በተፈጠሩበት ቅፅበት በቶሎ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ከሲዳማዎች የሚጠበቅ ነው። ሲዳማዎች መሀመድ ናስር እና ሚሊዮን ሰለሞንን በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ የሆኑባቸው ሲሆን ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ከጉዳት የሚመለስ ይሆናል፡፡ የመሀመድን አለመኖር ተከትሎም ሀብታሙ ገዛኸኝን በመሀል አጥቂነት ሊሰለፍ የሚችልበት ዕድል ይኖራል።

አጥቅቶ በመጫወት የማይታሙት ደቡብ ፖሊሶች ከተጋጣሚያቸው ባህሪ አንፃር ነገ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ሊወስዱ ቢችሉም በሙሉ ኃይላቸው ያጠቃሉ ተብሎ ግን አይገመትም። በይበልጥ ደግሞ የቡድኑ የመስመር ተከላካዮች የሲዳማን የመስመር አጥቂዎች ለመቆጣጠር ወደራሳቸው ሜዳ መሳባቸው የሚቀር አይመስልም። በመሆኑም በዘላለም ኢሳያስ የሚመራው የአማካይ ክፍል ከሦስትዮሽ የአጥቂ መስመሩ በተለይም ከመስመር አጥቂዎቹ እገዛን ሊፈልግ ይችላል። በዚህም አስፈሪነቱ የሲዳማን ያህል ባይሆንም በአንዳንድ አጋጣሚዎች መልሶ ማጥቃትን እንደ አማራጭ ሲጠቀም የሚታየው ቡድኑ ነገም ጫና ከተፈጠረበት እና መሀል ላይ ኳስ የመያዙ ነገር ካልተሳካለት ሄኖክ አየለን መዳረሻ ያደረጉ ቀጥተኛ ኳሶች እንዲሁም የመስመር አጥቂዎቹ ላይ ትኩረት ያደረጉ ድንገተኛ ጥቃቶችን መፈፀምን እንደ አማራጭ እንዲወስድ ሊያደርገው ይችላል። በዚህ ረገድ የየተሻ ግዛው ከጉዳት መመለስ ለአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ መልካም ዜና ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ ብርሀኑ በቀለ ፣ አበባው ቡታቆ እና ኤርሚያስ በላይ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በእስካሁኑ ሦስት የሊግ ግንኙነታቸው ደቡብ ፖሊስ ድል አልቀናውም። ሲዳማ ቡና ወደ ሊጉ በመጣበት እና ደቡብ ፖሊስ በወረደበት የ2002 የውድድር ዓመት ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ አንዱን አሸንፎ በሁለተኛው ነጥብ ሲጋሩ የዘንድሮው ጨዋታቸውም በሲዳማ 4-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር።

– በሜዳቸው ሽንፈት ካልገጠማቸው ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ሲዳማ ሀዋሳ ላይ 13 ጨዋታዎችን አድርጎ አስሩን በድል ሲወጣ በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎችም ነጥብ መጋራት ችሏል። በሜዳው ነጥብ ከጣለም ሰባት ጨዋታዎች አልፈዋል።

– በተመሳሳይ ሀዋሳ ላይ 13 ጨዋታዎችን ያደረገው ደቡብ ፖሊስ አራት ጊዜ ድል አድርጎ አንዴ ነጥብ ከመጋራቱ ውጪ በቀሪዎቹ ስምንት ጨዋታዎች ግን ምንም ነጥብ ማሳካት አልቻለም።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ይህን ጨዋታ የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል። አርቢትሩ ሲዳማን ከጊዮርጊስ (ሁለት ጊዜ) የዳኘ ሲሆን ሁለቱ ተጋጣሚዎች ከሀዋሳ የተጫወቱባቸውን ጨዋታዎችም መርቷል። ኃይለየሱስ በእስካሁኖቹ ዘጠኝ ጨዋታዎች 21 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ሲያሳይ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችን የሰጠ ሲሆን አንድ ጊዜ ደግሞ ሁለተኛ የቢጫ ካርድን መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

ዮናታን ፍሰሀ – ፈቱዲን ጀማል – ግሩም አሰፋ – ሰንደይ ሙቱኩ

ግርማ በቀለ – ዮሴፍ ዮሃንስ – ወንድሜነህ ዓይናለም

ይገዙ ቦጋለ – ሀብታሙ ገዛኸኝ – አዲስ ግደይ

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

መክብብ ደገፉ

አናጋው ባደግ – ደስታ ጊቻሞ – ዘሪሁን አንሼቦ – ዘነበ ከድር

ዘላለም ኢሳያስ – ዮናስ በርታ – ኪዳኔ አሰፋ

የተሻ ግዛው – ሄኖክ አየለ – ብሩክ ኤልያስ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡