የኢትዮጵያ ቡና ጋዜጣዊ መግለጫ

ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ከመቐለ 70 እንደርታ ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ ሳይካሄድ መቅረቱን ተከትሎ በቀጣዩ ቀን በዝግ እንዲካሄድ መወሰኑን በመቃወም ሰኞ 09:00 ላይ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የክለቡ ፕሬዝዳንት መ/አለቃ ፍቃደ ማሞ ፣ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ በቀለ የደጋፊ ማኅበሩ ፕሬዝደንት አቶ ክፍሌ አማረ እና ም/ፕሬዝደንት አቶ ሰለሞን እንዲሁም በርከት ያሉ የሚዲያ አካላት በተገኙበት በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በመግለጫው ተካሂዷል።

መቶ አለቃ ፈቃደ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ” በአጭር ጊዜ ውስጥ ያደረግነውን ጥሪ ተቀብላቹ ስለመጣቹ ምስጋናችንን እናቀርባለን። እሁድ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም የነበረን ጨዋታ እኛ በማናቀው እና ባልተረዳነው ሁኔታ እንዳይከናወን ተደርጓል። ከዚህ በኃላ ፌዴሬሽኑ ማምሻውን ተሰብስቦ (ያልተፈራረሙበት እንደሆነ መረጃ ስላለን ነው) ጨዋታው ወደ አዳማ እንዲካሄድ እና በዝግ እንደሚደረግ ወስነው ወጥተዋል። ይህም ውሳኔ ከመመርያ እና ከውድድር ደንብ ውጭ መሆኑን ገልፀን ውሳኔውን እንደማንቀበል አስፈላጊውን መልስ በደብዳቤ አሳውቀናል። ግልባጭ ለፌደራል ፖሊስ፣ አአ ፖሊስ፣ ለኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን፣ አአ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ለአስራ አምስቱ የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ይህ ውሳኔ እንዲደርሳቸው አድርገናል። አሁን ስለ እሁዱ ጨዋታ ከመነጋገራችን በፊት ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር በመቐለ ከተማ ላይ ያደረግነውን ጨዋታ አስመልክቶ በበቦታው የተገኙ ሰዎች ስላሉ ስለዛ ጨዋታ እንዲያስረዱ እድል እሰጣለው።” ብለዋል።

አቶ ስንታየሁ በቀለ ስለ መቐለው ጨዋታ

ኢትዮጵያ ቡና ወደ መቐለ ሲጓዝ አንድ የልዑካን ቡድን ክለቡ በወሰደው ፍቃድ ተጉዟል። በፌዴሬሽኑ በኩል ፕሬዝደንቱ፣ ሌሎች የስራ አስፈፃሚ አባላት ወደ ስፍራው ተጉዘዋል። የሄድንበትም ምክንያት ከዚህ በፊት ተፈጥረዋል የተባሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ነው። መቐለ እንደደረስን ወድያውኑ ማለት ይቻላል ከፕሬዝደንቱ ጋር ተገናኝተን የእነርሱ የክለቡ አመራሮች፣ የክልሉ ፌዴሬሽን ተወካዮች፣ የክለቡ የደጋፊ ማኅበር አመራሮች እና ሌሎችም በተገኙበት ስብሰባ አደረግን። ሁለቱ ወንድማማቾች ክለብ መካከል መጨቃጨቅ እና አንዳንድ ሁኔታ ተፈጥሯል ተወያይተን እንፍታው በማለት ረጅም ሰዓት የፈጀ ውይይት አድርገናል። የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ፎቶ በስቴዲየም ገንጥላችኃል ተባልን። በእኛ በኩል ፈፅሞ አላደረግንም ፣ አልቀደደንም። በወቅቱ ከባድ ዝናብ ውንሽንፍር የቀላቀለ ስለነበረ እርሱ ይሆናል እንጂ እኛ ይህን አላደረግንም። ይህ ለምን ይሆናል እሳቸው ለሁላችንም ጠቅላይ ሚንስቴር ነበሩ። ለምንድነው አካባቢን (የተወለዱበትን ቦታ) ተለይቶ እየተቆፈረ የሚነሳ ከሆነ የት ነው የምንደርሰው ተገቢ አይደለም። ሆን ተብሎ የተደረገ ነገር የለም። ይህ የተደረገው ሆን ተብሎ ነው ብላቹ ከወሰዳቹ ለሠላሙ ስንል ለወንድማማችነት ሲባል ይቅርታ ጠይቀናል አለን። ቀግሎም የሚዲያ አካላት በተገኙበት መግለጫ እንድንሰጥ ተደረገ።

በማግስቱ ጨዋታ ነበር፤ ቅድመ ስብሰባም በሠላም ተጠናቋል። አሁን ትልቁ ችግር የተፈጠረው ወደ ሜዳ ስንገባ ነው። መጥቀስ የማልችለው በጣም የሚሰቀጥጥ ዛቻ ስድብ ባላሰብነው ሁናቴ ይንፀባረቅ ጀመር። ከደቂቃዎች በኋላ ከስቴዲየሙ ውስጥ በባነር የተፃፈ ፅሁፍ መጣ። የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር ፎቶ ያለበት “ቡና ይሁዳ መለስን የከዳ” ይላል በወቅቱ የነበሩት የስፖርቱ ከፍተኛ አመራሮች በሁኔታው ደንግጠዋል። ጨዋታው ተካሂዶ ኳሱ ላይ ሳናተኩር ጨዋታው አለቀ። የስፖርቱ አመራሮች ሁኔታውን በዓይናቸው አይተዋል። ይህ ለእግርኳሳችን የማይበጅ ስለሆነ እርምት ይደረግበት በማለት ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ አስገባን። ምንም ምላሽ አልተሰጠንም። ከስር ከስር መመለስ የነበረበት ጉዳይ እየተንከባለለ እዚህ ደርሷል። አሁን ደግሞ ጨዋታ አለን ብለን ሄድን። ተሰርዟል ተባለ። እኛ ላይ ከፍተኛ ቅጣት ተጥሎብናል።

አቶ ሰለሞን (የደጋፊ ማኅበር ም/ፕሬዝደንት)

እኛ መቐለ በሄድንበት ወቅት ለህዝቡ የተነገረው መረጃ የተሳሳተ ነበር። ክቡር ጠቅላይ ሚንስቴራችንን የያዘ ባነር ተቀዶ እንደተቃጠለ ነው ህዝቡ መረጃ የደረሰው። ይህ የተሳሳተ መረጃ ነው። በወቅቱ ከድሬደዋ ከተማ ጋር ስንጫወት ባነሩ ዝናብ እና ፀሀይ ተፈራርቆበት ስለነበረ ራሱ እንደተገነጠለ እና ምንም አይነት የፖለቲካ ሴራ እንደሌለ ማን እንዴት እንደተገነጠለው እንደማይታወቅ አስረዳን። እርሳቸው የሁሉም የኢትዮጵያ ልጅ ናቸው። ክለባችን ከፖለቲካ፣ ከዘር፣ ከሃይማኖት ነፃ ነው። ቡና ውስጥ ያሉት ደጋፊዎችም ሆኑ ሁሉም ተጫዋቾች ከተለያዩ ክልሎች ብሔር ብሔረሰቦች የተሰባሰቡበት ነው። ይህን ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያ ቡና ወደ መቐለ ከመጓዙ አስቀድሞ ብዙ ሙከራ አድርገናል። ሆኖም የመቐለ ደጋፊ ማኅበር ይህን ኃላፊነት አንወስድም በማለታቸው በዚህ ምክንያት ደጋፊዎቻችንን አልላክንም። በዚህም ምክንያት ለመጀመርያ ጊዜ የቡና ደጋፊዎች ከሚወዱት ክለብ እንዲነጠሉ አድርገናል።

መቐለ ስንሄድ የሆነውን አቶ ስንታየው ገልፀዋል። ከዛም በኃላ ወደ ሱሑል ሽረ ስንሄድ አራት መኪና በመያዝ የመቐለ ደጋፊዎች ሲቃወሙን ነበር። የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ ጨዋታ መዳረሻ ላይ በተለያዩ ሚዲያዎች ለመግለፅ እንደሞከርነው አስጊ ነገር አለ። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለቀቀው ነገር ጥሩ አይደለም። ጨዋታው ወደማያስፈልግ አቅጣጫ እንዳያመራ ለመቐለ ጨዋታ ደጋፊዎቻቹ አዲስ አበባ ባይገኙ ብለን ገልፀናል። ሆኖም ይህን የተናገርንበት መንገድ የተለየ ስሜት ኖሮን አይደለም። ፀጥታው ጉዳይ ስላሳሰበን ለሰላም ካለን ፍላጎት የተነሳ ነው እንጂ አዲስ አበባ አትምጡ ለማለት አይደለም። አአ የሁሉም ከተማ ናት ብለናል።

መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ

ያለው ዝርዝር ሁኔታ ይህን ይመስላል። የተዘነጋ ነገር አለ። ከመነሻው የመቐለ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ሽፈራው ጋር በሆነ ስብሰባ ተገነኝተን በሁለቱ ክለቦች መካከል ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች አሉ። ለምን ቁጭ ብለን ብንጋገር የሚል ሀሳብ አቀረቡ። እኛም ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በቦታው ተገኝተን እንድንነጋገር ተደርጓል። መነሻው ይሄ ነው። በዛ ውይይት ላይ ነገሩ እውነትም ሆነ አልሆነም ይቅርታ ጠይቁ ስለተባልን ይቅርታ ጠይቀናል። ክለባችን ይቅርታ የጠየቅበት ምክንያት ፈርቶ አይደለም። ውድድሩ የወንድማማቾች ሆኖ እንዲቀጠወል ለሠለም ካለን ፅኑ ፍላጎት ነው። ነገር ግን ይቅርታውን ጠይቀን በማግስቱ የተከሰተው ነገር የሚያሳዝን ነበር፤ እርሱን አልደግመውም ። ይህንን ጉዳይ ይዘን ወደ ፌዴሬሽኑ ስንሄድ ሌላ አዲስ ድራማ ጠበቀን። የጨዋታው ኮሚሽነር ሪፖርት ሲያስገባ አላየሁም፣ እንድያውም መቐለ ከተማ ይበጠብጡ የነበሩት የቡና ደጋፊዎች ናቸው። ዳኛውም አላየሁም አለ። ይህ ከፍተኛ ችግር ነው። እሺ ብለን ፍትህን የምትፈልጉ ከሆነ በቦታው አቶ ኢሳይያስ ጅራ ስነበሩ እርሳቸውን ጠይቁ ብለን ነበር። ቢያንስ መቐለን ባይቀጡ እንኳን ኮሚሽነሩ እና ዳኛውን ይቀጡ ነበር።

የኦሊምፒክ ፕሬዝደንት ዶ/ር አሸብር የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሸነሩ አቶ ርስቱ ይርዳው በወቅቱ ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ግዙፍ አመራሮች ኖረው ፌዴሬሽኑ አላየሁም አልሰማውም ብሎ ሽምጥጥ ነው ያደረጉት። ለዚህም ከአንዴም ሁለቴ ሦስቴ በደብዳቤ ጠይቀናል መልስ አልሰጡም። በግሌም ፕሬዝደንቱን ይህ ለእግርኳስ አደገኛ ነው። በፊፋም ሆነ በእኛ የውድድር ደንብ ሜዳ ውስጥ ፖለቲካ ማፀባረቅ አይቻልም። ስለዚህ ምላሽ የማትሰጡን ከሆነ ወደ ስፖርት ገላጋዮች ፍርድ ቤት እንሄዳለን ብያለው። በዚህ ሳምንት ደብዳቤያችንን እናስገባለን።

የእሁዱ ጨዋታ ሲደርስ 150 በላይ አስተናጋጆች አሉን። እንደምታቁት ይህን ጨዋታ ማስተናገድ ከባድ ነው። ምን ሁኔታ ሊፈጠር አንደሚችል ስለማይታወቅ አናስተናግድም አሉን። እኛ በዚህ ሁኔታ ፀጥታው ይረጋገጣል ማለት ከባድ ነው ብለን የመቐለ ደጋፊ እንዳይመጣ በሚል ለፖሊስ አሳውቀናል። ሆኖም ባለ ሜዳ እኛ ሆነን ሳለ ሳይማክሩን በራሱ ፍቃድ ከመቐለ ክለብ ጋር የሚሰራ ኮሚቴ አዋቅረው የስቴዲየም መቀመጫዎችን ሲደለድሉ እንደነበረ አውቀናል። ጥቂት ቆይተው ደግሞ ጥቂት ደጋፊ ከገባ በኃላ እንዲዘጋ አደረጉ። ማን እንደወሰነ አናውቅም በፌዴሬሽኑ በፈላጭ ቆራጭነት ሳያማክረን ወሰነ። ጭራሽ ” ጨዋታው በዝግ በአዳማ ከተማ ላይ እንድንጫወት ተወስኗል” የሚል ደብዳቤ ደርሶናል። እኛም ይህን ውሳኔ በጭራሽ አንቀበልም በማለት አሳውቀናል። ጉዳዩን ይዘን ወደ ካስ ሁለተኛ ተደራቢ ክስ ይዘን ፌዴሬሽኑን ለመክሰስ እናመራለን። ከአሁን በኃላ ወደ ኃላ መመለስ የለም ። ሀገር መከሰሷ እናዝናለን ግን ሀገርን ወክለው የተቀመጡ ሰዎች ክለቦች እርስ በራሳችን እንድንበላላ የኢትዮጵያ እግርኳስ እንዲወድቅ ፍላጎት ያላቸው አካላት መታረም ይኖርባቸዋል። አሁን የሚያሳብቡት ፖሊስ አዞናል ነው የሚሉት። ፖሊስን ስንጠይቅ ደግሞ አትጫወቱ የሚል ውሳኔ ከእኛ አልወጣም እያሉ ነው። ስለዚህ ፌዴሬሽኑ ባለቤት አልባ ነው።
ነገሮችን እንለደፋቸው ብለን እንጂ ባለፈው ከሀዋሳ ጋር ወታደራዊ ካምፕ ውሰጥ የሊግ ውድድርን ማጫወት ህገ ወጥ ነው። በፊፋ ህግ እና ደንብ አይፈቅድም። ደጋግሜ የምነግራችሁ ኢትዮጵያ ቡና ነገ ወደ አዳማ በመሄድ የሚያደርገው ጨዋታ እንደማይኖር ነው። ፌዴሬሽኑ ይህን ውሳኔያችንን የማይቀበል ከሆነ ለክለቡ ህልውና ስንል ፊፋ እና ካስ ይዘነው እንሄዳለን። አንድ ሚሊዮን ብር ከተመልካች ገቢ አጥተናል። ካስን እንጠይቃለን።

ከሚዲያ አካላት የቀረቡ ጥያቄዎች

እንደሚታወቀው የእግርኳሱ አስተዳደር ችግሩ ብዙ ነው። አቶ ኢሳይያስ እንዲመረጡ ደግሞ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጋችኋል። በዚህ ነገር አሁን ትፀፀታላችሁ ?

መቐለ አሉ በሚባሉ የመንግስት ባለስልጣን ባሉበት ምስክር በማያሻ ሁኔታ ይህ ሁኔታ ሲፈጠር ቅጣት አለመጣል የእግርኳስ አስተዳደር ብቃት ማነስ ነው?

ከፎርማት ለውጥ ጋር ተያይዞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፕሬዝደንት ከአቶ አብነት ገብረመስቀል ጋር ተነጋግራችኃል?

የፌዴሬሽኑን ውሳኔ እንደማትቀበሉ አሳውቃችኋል። ፌዴሬሽኑ ይህን ተከትሎ እርምጃ ቢወስድ፤ ቅጣት ቢያስተላልፍ ቀጣይ እርምጃቹ ምንድነው? ራሳችሁን ከውድድሩ ታገላላቹ?

እናንተ አልጫወትም ብላቹ ቢቀር፤ የዚህ ጨዋታ ውሳኔ በሌሎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ከግምት አስገብታችኋል?

ምላሾች

መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ

– ሲመረጥ ደጋፊ ነበራቹ ለተባለው – አዎ። የፌዴሬሽን ምርጫ ሰመራ ከተማ ሲደረግ ከአንድ ሰው በቀር እንዲመረጡ ከፍተኛ ቅስቀሳ አድርገናል። ይህ ደግሞ ማንም እንደሚያደርገው እከሌ ቢመረጥ የተሻለ ነው በሚል ነው። እንደምታውቁት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ ሲመረጡ ተቀባይነት ነበራቸው። ትናንት በተለይ ሲኤንኤን ላይ የመጨረሻ ውሸታም የመጨረሻ አጭበርባሪ ሰውዬ እያሉ ሲወርዱባቸው ነበር። ይህን ለምን አሉ? ይመስለኛል ከተግባራቸው ተነስተው ይመስለኛል። ስለሆነም በበቂ ሁኔታ መስራት ካልቻለ መቃወሙ አብሮ ያለ ጉዳይ ነው።

– አሉ በሚባሉ የመንግስት ባለስልጣን ባሉበት ምስክር በማያሻ ሁኔታ ይህ ሁኔታ ሲፈጠር ቅጣት አለመጣል የእግርኳስ አስተዳደር ብቃት ማነስ ነው። ለተባለው መልሱን በቀጥታ አልመልስም በማለት በምሳሌ አብራርተው ፌዴሬሽን ውስጥ እንዲህ ብል እንዲህ ይሆናል የሚል ችግር አለ።

– አሁን ያለው ፎርማትን እኛ አንስማማበትም። የማንስማማበት ምክንያቶች ብዙ ናቸው። ሲጀመር ፎርማቱን ያፀደቀው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ሳይሆን መንግስት ነው። በወቅቱ ሲቃወሙት የነበሩት የተወሰኑ ጋዜጠኞች እና የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለሁለት ዓመት ታግሏል። እንደሚታወቀው አብዛኛዎቹ ክለቦች የመንግስት በጀት የሚመደብላቸው ናቸው። በጀቱ እንዴት እንደሚከፋፈል አይታወቅም። የሙስና ስራ ይሰራበታል። ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ተዟዙሮ መጫወት ከባድ ሆኗል። የጎጥ ፖለቲካው መንደር ድረስ ወርዷል። እግርኳስ ህዝብን የሚያቀራርብ ፣ የሚያፋቅር ሆኖ ሳለ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እንዲያውም ሀገሪቷ እንዳትረጋጋ እያደረገ ያለው ኳስ ነው። ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ በአንድ ክልል ሆነው በሜዳቸው ሲያቅታቸው አአ እንዲጫወቱ ከመፍቀድ ውሳኔ ሰቶ በሜዳቸው እንዲጫወቱ አለማድረጉ ፌዴሬሽኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ጎጠኝነት እንዲስፋፋ ከሚፈልጉ ክለቦች ጋር እየወገነ ነው የሚመስለው።

– የትኛው ቡድን ነው በዚህ ውድድር አትርፎ እየተንቀሳቀሰ ያለወ? አንድም ክለብ የለም ። እንዲያውም ሀገሪቱን ገንዘብ ለመዝረፍ አመቺ ሆኗል። ለትራንስፖርት ፣ ለሆቴል ሲወጣ አንዳንዴ እኮ ደረሰኞቹ ላይ ስህተት ይሰራሉ ። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች እስኪስተካከሉ ድረስ አንድ አምስት ዓመት የመረጋጊያ ጊዜ ያስፈልገናል። ሁላችንም በየሰፈራችን የጎጥ ፖለቲካ በሚሞትበት ጊዜ በነፃነት በወንድማማችነት ወደምናራምድበት የእግርኳስ ውድድር ውስጥ እንግባ ነው የእኛ አቋም።

– ከአቶ አብነት ጋር ተነጋግረሀል ለተባለው ብነጋገርም ባልነጋገርም ከእኔ ጋር ከማይስማማው ጋር ጥሩ ሀሳብ ይዞ ከሚመጣው ጋር ተስማምቼ እሄዳለው። ምን መደረግ እንዳለበት የእኛን አቋም ተዟዙሮ መጫወት ይቁም ሁላችንም ወደ የሰፈራችን እንግባና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጥረት እናጥፋው። የተሻለ ነገር ሲመጣ በዘመናዊነት እንመለስ ነው የእኛ አቋም።

– የአዳማ ጨዋታ ብትቀጡ ለተባለው አንሄድም አለቀ በቃ ቢቀጣን ደግሞ የምንሄድበት እንሄዳለን። ራሳችሁን ከውድድሩ ታገላላቹ? ለምን እንገለላለን? ድሮ እንዲህ እንል ነበር። አሁን አንልም። ወደሚያስፈልገው አካል እንሄዳለን። ከተሳሳትን እንታረማለን። ካሸነፍን ደግሞ አሸነፍን ነው።

-በሌሎች ክለቦች ላይ የሚደርሰውን ተፅእኖ አይተናል። ነገር ግን እኛ አዳማ አንሄድም የምንለው ለሌሎችም ክለቦች ግልፅ እኩል ውጤት እንዲገኝ ስንል ነው። አሁን ይሄ ሁሉ እየተደረገ ያለው ቡና ደካማ ቡድን ነው ጥንካሬው ደጋፊው ነው። ስለዚህ ደጋፊው በሌለበት እናዘጋውና እኛ እናሸንፋለን ብለው ያሴሩት ግልፅ ነው። የሞኝ ሴራ ነው። እውነት ነው የምላቹ የሞኝ ሴራ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡