አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የአሰግድ ተስፋዬ አካዳሚን ጎብኝተዋል


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና እና ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አሰግድ ተስፋዬ የተመሰረተው የአሴጋ የእግር ኳስ አካዳሚ በመገኘት ታዳጊዎቹን ጎብኝተዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከተሰጣቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በተጨማሪ በግላቸው በበርካታ የሀገራችን ከተሞች በመገኘት የታዳጊ የእግር ኳስ ማሰልጠኛዎችን እየተመለከቱ የሚገኙት የካፍ ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ ዛሬ ረፋድ ላይ ደግሞ በቀድሞው የኢትዮጵያ ቡናና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አሰግድ ተስፋዬ ስም የተቋቋመውን ከ13 እና 15 አመት በታች የዕድሜ ዕርከን ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾችን ያቀፈው አሴጋ የእግር ኳስ አካዳሚን ሾላ በሚገኘው የማሰልጠኛው ሜዳ በመገኘት ለታዳጊዎቹ ምክር እንዲሁም በቀጣይ ድጋፍን ለማድረግ ማሰባቸውን ገልፀውላቸዋል፡፡

በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ሁለት ዓመት የሆነው የአካዳሚው መስራች አሰግድ ተስፋዬን የምናስታውሰው እሱ የጀመረውን መልካም ተግባር በመደገፍ እና ከጎኑ በመቆም በማሳየት እንደሆነ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል “የአሰግድ አላማ እሱን የሚተኩትን ማፍራት ነበር። እሱ ባይኖርም ራዕይው ስላልሞተ በርትተው እንዲሰሩ ማድረግ የሁሉም ሰው ግዴታው ነው።” ብለዋል። አሰልጣኙ አክለውም “ከሌሎች አካዳሚዎች የአስጌ የሚለይበት ምክንያት ትምህርታቸውን በሚገባ የሚከታተሉ ጎበዝ ልጆች አሉበት። ከወላጆች ጋርም ግንኙነቱም ጥሩ ነው። ይህ ደግሞ ለልጆቹ የወደፊት ተስፋ ስንቅ ነው። ምንም እንኳን አሰግድ በህይወት ባይኖርም ባለቤቱ እና የአሰልጣኙ ወዳጆች አካዳሚው እንዲቀጥል በማድረጋቸው ምስጋና ይገባቸዋል።” ብለዋል፡፡

የአሰልጣኝ አሰግድ ባለቤት ወይዘሮ ገነት ባስተላለፉት መልዕክት ደግሞ የአንድ ሀገር አሰልጣኝ ወደ አካዳሚው መጥቶ በመጎብኘቱ ደስተኛ መሆኗን ገልፃ በተጨማሪም የአካዳሚው አሰልጣኞች በቂ እውቀት እንዲኖራቸው የማሻሻያ የአሰልጣኝነት ስልጠና እንዲወስዱ ጥያቄ ቢጠይቁም ምላሽ ሳያገኙ እንደቆዩና አሁን ላይ ግን ለማመቻቸት ስላሰቡ አመስግነዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: